አምባ ዲጂታል፤ ሐሙስ ጥር 11፣ 2015 ― የብር የመግዛት አቅም ከሌሎች የውጭ መገበያያ መገበያያ ገንዘቦች አኳያ ሊዳከም ነው መባሉን ያስተባበሉት የመንግሥት ሹም የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የብር የመግዛት አቅም ሊዳከም ነው በሚል በሥፋት እየተወራ መሆኑን የገለጹት ኢዮብ፤ ሆኖም ጉዳዩን ‹‹ፈጽሞ መሠረተ ቢስ›› ብለውታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ብርን ከዶላርና ከሌሎች የውጭ መገበያያ ገንዘቦች አኳያ የማዳከም እቅድ እንዳለው ባለፉት ሳምንታት በሥፋት ሲናፈስ ቢቆይም፤ ከመንግሥት ወገን ሳይሰጥበት ቆይቷል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ መንግሥት የብር አቅም እንዲዳከም (Devaluation) ውሳኔ ያስተላለፈው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን ነበር፡፡ በወቅቱ ብር ከዶላር አንጻር በ15 በመቶ እንዲዳከም ተደርጓል፡፡ ከዚያም የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር የውጭ ምንዛሪው ገበያን መሠረት በማድረግ (Depreciation) የብር አቅም እንዲዳከም አድርጎታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ አንድ ዶላር 27 ብር አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ በየዓመቱ ቢያንስ በ25 በመቶ እንዲዳከም ተደርጎ በአሁኑ ሰአት ከ53 ብር በላይ ደርሷል፡፡
መንግሥት የብርን የመግዛት አቅም ከዶላር እና ሌሎች ገንዘቦች አንጻር የማዳከም ውሳኔ፤ ከጀርባው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ግፊት እንዳለበት በሥፋት ይነገራል፡፡ በቅርብ ጊዜ በወጡ መረጃዎች የተቋማቱ ባለሞያዎች የኢትዮጵያ ገበያ በአሁኑ ሰአት እየተመራ የሚገኘው በመደበኛው የምንዛሬ ተመን ሳይሆን፤ በትይዩ (በተለምዶው ጥቁር ገበያ) ስለሆነ ብርን ማዳከም ገበያው ላይ የሚፈጥረው ጫና የለም መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ ሆኖም የብርን አቅም ማዳከም የዋጋ ግሽበትን ከማባባስ ባለፈ ሚና ሊኖረው አይችልም የሚሉ ባለሞያዎችም አሉ፡፡ በተጨማሪም በነባሩም ሆነ በአዲሱ የመንግሥት አስተዳደር የብርን አቅም ከዶላር አንጻር የማዳከም ፖሊሲ ዓላማው፣ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለመጨመርና የገቢ ንግዱን ደግሞ ለመቀነስ በሚል ቢሆንም፤ ይህ አለመሳካቱን የቁጥር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡