Saturday, May 18, 2024
spot_img

መንግሥት ብርን በየዕለቱ የማዳከሙ አሠራር መቀጠል አለመቀጠሉን ለመወሰን የዳሰሳ ጥናት እያካሄደ መሆኑ ተሰማ

  • አሠራሩ ከጀመረበት 2012 መጀመሪያ አንስቶ የአንድ ዶላር ከብር ጋር ያለው ምንዛሬ በ21 ብር ልዩነት አሳይቷል

(አምባ ዲጂታል) ሰኞ የካቲት 7 2014 ― የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የኢኮኖሚ ተሐድሶ ፕሮግራም ተግባራዊ የሆነውን የብር የምንዛሪ አቅምን በማዳከም የውጪ ንግድን የማሳደግ አሰራር ዕጣ ፋንታ ላይ ለመወሰን የዳሰሳ ጥናት እያካሄደ መሆኑን ተሰምቷል፡፡

ዋዜማ ራድዮ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከፍተኛ የስራ ሐላፊን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ብርን ከሀገሪቱ የንግድ ሸሪኮች መገበያያ ገንዘብ አንጻር እየተተገበረ ያለውን ዕለታዊ ዋጋ የማዳከም አሰራር የሚገመግም የዳሰሳ ጥናት እየተሰራ ይገኛል። በጥናቱ ላይ በመመርኮዝም ብርን በየዕለቱ የማዳከሙ ነገር ‹‹ይቀጥል›› ወይንስ ‹‹አይቀጥል›› የሚለው ላይ ከውሳኔ ይደረሳል።

ዕለታዊ የብርን የውጭ ምንዛሬ ተመን ከንግድ አጋር ሀገራት መገበያያ አንጻር በፍጥነት የማዳከሙ እርምጃ ከሁሉም የማክሮ ኢኮኖሚ መመዘኛዎች አንጻር የማያዋጣ ከሆነ ብሄራዊ ባንኩ ሌሎች አማራጮችን ለመከተል ይገደዳል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከ2012 ጀምሮ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚል ስያሜ እየተገበረ ባለው የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን አሰራር፣ የኢትዮጵያን ብር ትክክለኛ ዋጋውን እንዲያገኝ እና የወጪ ንግድን ለማሳደግ ይረዳል በሚል የብርን የምንዛሬ ተመን ከንግድ አጋር ሀገራት ተመን አንጻር እያዳከመ መጥቷል።

ዕለታዊው ፈጣን ምንዛሬን የማውረድ እርምጃ ከ2012 ተጀምሮ በተያዘው ዓመት 2014 እንዲያልቅና ኢትዮጵያ በገበያ የሚመራ የምንዛሬ ተመን እንዲኖራትም ታስቦ ነው ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው።

እርምጃውን ተከትሎ በ2012 መጀመርያ ላይ አንድ የአሜሪካን ዶላርን በባንክ ሲቀርብበት ከነበረው 29 ብር አሁን ዋጋው ወደ 50 ብር ከ32 ሳንቲም አድጓል። በነዚህ ጊዜያት የኢትዮጵያ ብር የምንዛሬ ተመን ከዶላር አንጻር በ21 ብር ገደማ እንዲዳከም ተደርጓል። 

አሁን መንግስት እየተከተለ ያለው የምንዛሬ ተመን አሰራር የገቢ እቃዎችን ዋጋ በማስወደድ የዋጋ ንረትን የፈጠረ በመሆኑ ይተቻል። የምንዛሬ ተመኑ ተግባራዊ ከተደረገ አንስቶ የየወሩ አጠቃላይ የዋጋ ንረት ከ20 በመቶ በላይ ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ ከ30 በመቶ በላይ ሆኗል። የጥር ወር የዋጋ ንረት 34 በመቶ ሲሆን የታህሳስ ደግሞ 35 በመቶ እንደነበር ይታወሳል። 

ብሄራዊ ባንክ እያደረገ ያለው ጥናት በቀጣይ ዓመት አሁን ያለውን የምንዛሪ ተመን አሰራር ባለበት ለመቀጠል አልያም የተለየ መንገድ ለመምረጥ ዐቢይ መንገድ አመላካች ሆኖ እየተጠበቀ ይገኛል።

የምጣኔ ሐብት ፖሊሲ ባለሞያዎች የኢትዮጵያን መንግስት አካሄድ ከእነ አለም ባንክና አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር ለማግኘት በጫና የወሰደው እርምጃ እንጂ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሊባል አይችልም ሲሉ ትችት ሲሰነዝሩም ይደመጣል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img