Friday, May 3, 2024
spot_img

በአማራ ክልል በምዕመናን ላይ ግድያ፣ እገታ፣ ዝርፊያ እና መፈናቀል መድረሱን መጅሊስ ገለጸ

አምባ ዲጂታል፤ ማክሰኞ ሚያዝያ 1፣ 2016 – የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአማራ ክልል በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ግድያ፣ እገታ፣ ዝርፊያና ማፈናቀል መድረሱን የገለፀው ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 1 በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ነው።

ምክር ቤቱ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በታጣቂዎች እየተፈፀሙ የሚገኙትን፣ በተለይ ሙስሊሞችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እየተከታተለ እንደሚገኝም አስታውቋል። ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለእነዚህ ጥቃቶች በማሳያነት የጠቀሰው መጋቢት 29፣ 2016 ምሽት በባህር ዳር ከተማ፣ ከቀበሌ 14 መስጂድ የመግሪብ ሰላታቸውን ሰግደው እየወጡ በነበሩ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት (አንድ አባትና ሦስት ልጆቻቸው) ላይ ተፈጽሟል ያለው ግድያ ይገኝበታል። በዚህ ጥቃት ከቤተሰብ አባላት በተጨማሪ ጎረቤታቸው የሆነ ሌላ አንድ ግለሰብ በታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉንም አመልክቷል።

በተመሳሳይ በሞጣ ከተማ በአንድ ምዕመን ላይ ግድያ መፈፀሙንና በጎንደር ከተማ ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙን፤ መስጅድን በጥይት መምታት ቦምብ መወርወር በተደጋጋሚ ጊዜ እየተፈፀመ እንደሚገኝም ምክር ቤቱ አሳውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በአማራ ክልል ሞጣ ከተማ ታጣቂዎች አንድን ወጣት ካገቱ በኋላ፣ ቤተሰቦቹን በማስፈራራት 300 ሺህ ተቀብለው ሲያበቁ ታጋቹን በጭካኔ መግደላቸውንም የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መረጃ ይጠቁማል፡፡

በሁለቱ ከተሞች ከተፈጸሙት የግፍ ግድያዎች በተጨማሪ መጋቢት 26/2016 እንዲሁም ቅዳሜ መጋቢት 28/2016 በብቸና ከተማ ባል እና ሚስት በጥይትና በስለት እጅግ ዘግናኝ በሆነ መንገድ ግድያ የተፈፀመባቸው እና በጎንደር ከተሞች ስላማዊ ምዕመናን መገደላቸው በዚህ መግለጫ ተካቷል።

ከእነዚህ በተጨማሪ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ስምንት ወራት፣ በተለይ ሙስሊሞችን ዒላማ በማድረግ ግድያዎች፤ እገታዎች፤ ዘረፋዎች እና የማፈናቀል ተግባራት ሲፈፀሙ መቆየታቸውን የጠቆመው ምክር ቤቱ፣ የተለያዩ ሃይማኖትና እምነት ተከታዮች ለአያሌ ዘመናት አብረው በሰላም በኖሩባት ሀገር፣ ዜጎችን በሃይማኖታቸው ሳቢያ ልዩነት በመፍጠር የጥቃት ዒላማ ማድረግ፣ የሀገርን ሰላም እናየሕዝብን አብሮነት በእጅጉ የሚጎዳ፣ አስከፊ ማኅበራዊ ጠባሳ የሚያስከትል፣ ኃላፊነት የጎደለውና በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ሲል አውግዞታል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img