Friday, May 3, 2024
spot_img

የኢሳት ዐስረኛው ስንጥቅ

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) የተመሠረተው ከ13 ዓመት በፊት በሚያዝያ 2002 ነበር። ጣቢያው በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ኤርትራ ከትሞ የነበረው የግንቦት 7 ልሳን ሆኖ እስከ 2010 ድረስ አገልግሏል። በዚህ የኢሳት ጉዞ በእለት ተእለት ፕሮግራሞች ላይ የተለያዩ ጋዜጠኞችና ግለሰቦች ሠርተዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንጋፋው ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ ፋሲል የኔዓለም፣ መሳይ መኮንን፣ ደረጄ ሐብተወልድ፣ ግዛው ለገሠ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ተወልደ በየነ፣ ምናላቸው ሥማቸው፣ ሐብታሙ አያሌው፣ አበበ ገላው፣ ካሳሁን ይልማ፣ መታሠቢያ ቀፀላ፣ ገሊላ መኮንን፣ ኤርሚያስ ለገሠ እና ብሩክ ይባስ ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ጋዜጠኞችና በጣቢያው ዝግጅቶች አስተያየት በመስጠት የሚሳተፉ ግለሰቦች በ2010 ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ቀስ በቀስ የየራሳቸውን የዩትዩብ መገናኛ ብዙኃን እየመሠረቱ ወጥተዋል። ጋዜጠኞቹ እና ግለሰቦቹ ለአዲስ መገናኛ ብዙኃን ምሥረታቸው ምክንያት የሚያደርጉት የአካሄድ አለመግባባቶችን ነው። ከጣቢያው ወጥተው ከተመሠረቱት መገናኛ ብዙኃን መካከል በሐብታሙ አያሌው፣ ኤርሚያስ ለገሠ እና ብሩክ ይባስ የተከፈተው “ኢትዮ 360” በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

ከኢሳት ቦርድ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የነበረው የኢትዮጵያ ሚዲያ ሰርቪስ (ኢኤምኤስ) ሌላኛው ሚዲያ ሆኗል። ኢኤምኤስን የመሠረቱት በጣቢያው ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበራቸው ሲሳይ አጌና፣ ፋሲል የኔዓለም፣ መሳይ መኮንን እና ግዛው ለገሠ ነበሩ። ከዚህ በፊት እና በኋላ ርዕዮት ዓለሙ እና ተወልደ በየነ “ምንጊዜም ሚዲያ”ን ሲከፍቱ፣ ኤርሚያስ ለገሠ “አዲስ ኮምፓስ” የተሰኘ የዩትዩብ መገናኛ ብዙኃን ላይ እየሠራ ይገኛል። ከእነ ሲሳይ አጌና ጋር ኢኤምኤስን የመሠረተው መሳይ መኮንን “አንከር” የተባለ ሚዲያ እያንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፣ ራሱ ሲሳይ አጌናም ቢሆን በቅርብ ወራት “ሉዓላዊ” የተሰኘ ሚዲያ ሥራ አስጀምሯል።

በሌላ በኩል የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ ካሳሁን ይልማ ከአበበ ገላው ጋር ባንድነት “ኢትዮ ቮይስ ኔትወርክ”ን ሲከፍቱ፣ ደረጄ ሐብተወልድ የራሱን መገናኛ ብዙኃን ከፍቶ እየሠሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ በተጨማሪም ሌላኛው የኢሳት ባልደረባ ጋዜጠኛ ምናላቸው ሥማቸው ያለፉትን ጊዜያት ሄድ መጣ እያለ ከቆየበት ኢትዮ 360 ራሱን በመነጠል ግዮን ቲቪ የተሰኘ መገናኛ ብዙኃን ሊከፍት መሆኑን ትላንት ማክሰኞ ምሽት በኤክስ ገጹ ላይ አስታውቋል።

የቀድሞ ባልደረቦቹ ትተውት የሄዱት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኑ ይነገርለት የነበረው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንም ሚያዝያ ላይ 14ኛ ዓመት ከመድፈኑ አስቀድሞ፣ ድሮ የነበረው ተፅዕኖው ደብዝዞ ከራሱ ጋር አስረኛውን መገናኛ ብዙኃን አዋልዷል። [አምባ ዲጂታል]

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img