Friday, May 3, 2024
spot_img

ዐቢይ እና ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድ ከሮም መልስ ይነጋገሩ ይሆን?

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከ20 በላይ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በተሳተፉበት የጣሊያን – አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ሮም የገቡት ቅዳሜ እለት ነበር፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያን ‘ያኮረፉት’ የጎረቤት ሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድም እንዲሁ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከጉባዔው በፊት ሁለቱ መሪዎች ባንድ ስብሰባ ላይ መሳተፋቸው ትኩረት መሳቡ አልቀረም፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት ሶማሊያውያኑ እንደ መደፈር መቁጠራቸውን በሰልፍ እና በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ሲያስተጋቡት ቆይተዋል፡፡ ስምምነቱ ፕሬዝዳንቱ ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድን ‘ዐቢይ ከድተውኛል’ ያስባለም ነበር፡፡ ሐሰን፤ በዐቢይ ተከድቻለሁ ያሉት ከስምምነቱ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ስንገናኝ ይህን ሐሳባቸውን ደብቀውኛል በሚል ነው፡፡ ሐሰን ይህን ቢሉም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ሬድዋን ሑሴን፤ የስምምነቱን ቀን እና ዝርዝር ካልሆነ በስተቀር፣ ፍላጎታችንን የደበቅነው ጎረቤት የለም ሲሉ የሐሰንን ቅሬታ ውድቅ የሚያደርግ ንግግር ተናግረዋል፡፡

በርግጥ ዐቢይ እና ሐሰን ሮም ላይ በአንድ ስብሰባ ላይ ከመሳተፋቸው አስቀድሞ ውጥረቱ ስጋት ፈጥሮብኛል ያለው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አገራቱን የተመለከተt አጀንዳ ጠረጴዛው ላይ አስቀምጦ ስብሰባ ጠርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ዐቢይ በስብሰባው ላይ ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡ ዐቢይ በስብሰባው ላይ ላለመገኘታቸው የፕሮግራም መደራረብ በምክንያትነት ቀርቧል፡፡ በአንጻሩ ሐሰን የተሳተፉበት በኡጋንዳ ኢንቴቤ በተካሄደው ስብሰባ መጨረሻ ኢጋድ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመሃላቸው የተፈጠረውን ውጥረት እንዲያረግቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረሙትን የባህር በር መግባቢያ ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ላይ “ፈጣሪ ይመሥገን እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል” ያሉት ዐቢይ፣ ከኢጋድ ስብሰባ ቢቀሩም በንጋታው በዚያው አገር በተካሄደው የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ርዕሳነ ብሔር እና ርዕሳነ መንግሥታት 19ኛው ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ በተመሳሳይ የሶማሊያው መሪ ታድመዋል፡፡ የሶማሊያው መሪ ግን ከስብሰባው ወደ ቤት ሳይመለሱ ሌላ ቦታ ሄዱ፡፡

ሐሰን ከኢትዮጵያ ጋር ውጥረት ውስጥ ከገቡ በኋላ አለሁልህ ያሏቸው የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ የሆኑት የግብጹ ፕሬዝዳንት ዐብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር ሊመክሩ ወደ ካይሮ በረሩ፡፡ ሐሰን ካይሮ ከበረሩ በኋላ ከአል ሲሲ ጋር መክረዋል። እንደጠበቁትም በቆይታቸው በግብጽ ፕሬዝዳንት አይዞህ ተብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ በኩል የማይጠበቅ ባይሆንም የግብጹ ሰው ያስቆጣል ያሉትን ንግግርም አሰሙ። ከዚህ የሲሲ ንግግር በኋላ ሥም ባይጠቅሱም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አማካሪ ሬድዋን ምላሽ ሰጡ። ሬድዋን በኤክስ አንዳንዶቻችሁ እንዲህ የሚያደርጋችሁ ሶማሊያን ወድዳችሁ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ ያላችሁ ጥላቻ ነው አሉ። ሬድዋን በጽሑፋቸው፣ እኛ ዛሬ አለሁልሽ ለምትሏት ሶማሊያ ሲያስፈልግ ሕይወት ጭምር ነው የገበርነው ሲሉ አከሉ።

ይህ በእንዲህ ባለበት ነው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሶማሊያውን ፕሬዝንዳንት በድጋሚ ፊት ለፊት የሚያገናኘው የሮም ጉባዔ የመጣው። ዐቢይ ቅዳሜ ሮም ገብተው ሲያድሩ፣ ሐሰን ከተማዋ የገቡት እንደ ዐቢይ ቅዳሜ ሳይሆን ትላንት እሑድ ጥር 19፣ 2016 እኩለ ቀን ላይ ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ሮም ሲደርሱ ጥቂት ሰዓታት ቆይቶ ከከተማዋ የወጣው ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ‘የፋኦ አግሪኮላ‘ ሜዳልያ መሸለማቸው ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ዐቢይ ሜዳሊያ የማሸነፋቸው ዜና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን አየር ሞልቶ በሚኒስትሮቻቸው ‘አለቃ፣ እንኳን ደስ አለዎት’ ሲባሉ፣ እኩለ ቀን ሮም የደረሱት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ደግሞ አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጣይ ስለሚኖር ግንኘነት ወሬ እያስነገረ ነበር፡፡ የወሬው ነጋሪ ደግሞ የቪላ ሶማሊያ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዐብዱልቀፊር አሊ ዲግ ናቸው። ዳይሬክተሩ በንግግራቸው ከዚህ ቀደም የአገራቸው ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችውን ውል ትቅደድ፣ ይህ ሳይፈፀም ለየትኛውም ድርድር ቦታ የለንም አሉ። ዐብዱልቀፊር ይህን ሲሉ የኢትዮጵያ ሰዎች ምላሽ አልሰጡም። ባለሥልጣኑ የተናገሩት የሶማሊያ አቋም አዲስ ባይሆንም፣ ንግግሩ ከአንድ ቀን ቀድሞ ዐቢይ ከሰሞኑ ከሱማሌ ክልል ተወላጅ የሆኑትን ሚኒስትራቸውን አሕመድ ሽዴን ወደ ሞቃዲሾ ሊልኩ ነው በሚል የወጡ መረጃዎችን የሚያዳፍን መስሏል። የአሕመድ ወደ ሞቃዲሾ ማቅናት በመንግሥት በይፋ የተነገረ አይደለም። ሶማሊያም ቢሆን ከባለሥልጣናት ጋር ስለሚደረግ ንግግር ያለችው ነገር የለም። አሕመድ ሽዴ ወደ ሞቃዲሾ ያቀናሉ ከመባሉ አስቀድሞ፣ ከሶማሊያ የተነጠለችው የሶማሊላንድ መገናኛ ብዙኃን ዐቢይ ወደ እኛ ሊመጡ ነው አስብለው ነበር። ሶማሊላንዶች ያስነገሩት ጉዞ ግን እስካሁን አልተፈፀፀም።

በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ውጥረት የፈጠረው ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የባሕር በር ስምምነት አጀንዳነቱ ሳይበርድ አንድ ወር ሊደፍን ሁለት ቀን ብቻ ቀርቶታል። ስምምነቱ ፋታ የነሳቸው የሶማሊያው ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድ፣ ከስምምነቱ በኋላ ከሌሎች በተጨማሪ ኳታር እና አንካራም ደውለዋል። አስመራ እና ካይሮም በረዋል። ቀጣይ ጉዟቸው መፍትሔ ያስገኝላቸው ይሆን የሚለው የሚጠበቅ ሆኗል። አንዳንድ የአገሪቱ ፖለቲካ ተንታኞች ቀጣዩ ጉዟቸው ዐቢይ ‹‹ወንድሜ›› ወደሚሉት መሪ አገር ይሆናል የሚል መላ ምት አስቀምጠዋል። ነገር ግን ከመላ ምት የዘለለ ፍንጭ ቢያንስ እስካሁን አልታየም። [አምባ ዲጂታል]

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img