Tuesday, May 7, 2024
spot_img

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በጎንደር የደረሰው ጥቃት ‹‹በታጠቁ አክራሪ ክርስትያኖች›› የተፈጸመ ነው አለ


– ምክር ቤቱ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጥፋተኞች ተባባሪ ሆኗል ሲል ከስሷል


አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ሚያዝያ 19፣ 2014 ― የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ትላንት ሚያዝያ 18፣ 2014 በጎንደር የደረሰው ጥቃት ‹‹በታጠቁ አክራሪ ክርስትያኖች›› የተፈጸመው ነው ሲል በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡


ኢትዮጵያ ትላንትም ዛሬም ወደፊትም የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እና የበርካታ ሃይማኖቶች ሃገር ናት ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ፍላጎታቸው ‹‹በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት መስጂድን እና ሙስሊምን ሲያዩ ዓይናቸው የሚቀላ›› ያላቸው አካላት፤ በአማራ ክልል መስጂዶች መቃጠላቸውን እንዲሁም የሙስሊሞች ንብረት መውደሙን ጠቁሟል፡፡


ምክር ቤቱ ለአብነት ያህል በደቡብ ጎንደር እስቴ፣ እንዳባትና ጃራ ገዱ ከተሞች፣ በምስራቅ ጎጃም ሞጣ እና ቢቸና እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ የተቃጠሉ መስጆዶችን ዘርዝሯል፡፡ እነዚህን ድርጊቶች ለሀገር ሰላም ሲባል በታጋሽነት እና አርቆ አሳቢነት ታልፏል ያለው ምክር ቤቱ፣ ይህ ‹‹ፍርሃት የመሰላቸው ኃይሎች›› ‹‹ቆሻሻ›› ሲል ከገለጸው ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንዳልቻሉ ነው ያመለከተው፡፡


አያይዞም ትላንትም በጎንደር ከተማ በሸይኽ ኤልያስ ጥንታዊ የሙስሊም መቃብር ለቀብር የወጡ ሙስሊሞች ላይ የታጠቁ አክራሪ ክርስትያኖች በቡድን እና በነፍስ ወከፍ ትጥቅ ‹‹ጭፍጨፋ›› አድርሰዋል ብሏል፡፡


መካነ መቃብሩን በተመለከተም በተለያየ ሁኔታ ቦታውን ለመውረር ሰፊ ርምጃ ተካሄዷል ያለው ምክር ቤቱ፣ ‹‹ቦታው አንድ እና አንድ የሙስሊሞች መካነ መቃብር›› መሆኑንም በመግለጫው ጠቅሷል፡፡


አያየይዞም ‹‹እንደ ልባችሁ በተባሉ እና በመንግስት መዋቅር የሚደገፉ ኃይሎች ወንዝ ተሻግረው›› በእለቱ ሕይወታቸውን ያለፈ አባት ‹‹አናስቀብርም በማለት አስቀድመው ባዘጋጁት መሳሪያ ለቀብር በወጡ ሙስሊሞች ላይ በተኮሱት የመትረየስ የቦንብ ውርጅብኝ›› የሰዎች ሕይወት ማለፉን እንዲሁም ጉዳት እንደደረሰም ገልጧል፡፡


ምክር ቤቱ ይኸው ኃይል የጥቃት እንቅስቃሴውን በቀጥታ ወደ በከተማው በማድረግ በንግድ ተቋማት ላይ ኢላማውን በማድረግ በርካታ የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ሱቆችን ዘርፏል ያለ ሲሆን፣ መስጂዶችንና ሙስሊሞችን እየለየ በመደብደብ አገር የማተራመስ አላማውን ቀጥሎ አምሽቷል ብሏል፡፡


ጨምሮም ቀድሞም ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ እየተነገረው በቸልታ ተመልክቶታል ያለው የከተማው አስተዳደር፣ ችግሩን ፈጥኖ ለማርገብ ባለመቻሉ ምክር ቤቱ እስከ ፌዴራል ድረስ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ ኃይል ወደ ቦታው እንደደርስ በማድረግ ‹‹የአጥፊ ኃይሎቹ›› እንቅስቃሴ እንዲገታ መደረጉንም ነው ያመለከተው፡፡


የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በከተማው በሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ጥቃት በማውገዝ፣ በቀጣይ አስፈላጊውን የትግል ስልት በመቀየስ ሕዝባችንን በማስተባበር እንታገለዋለን ያለ ሲሆን፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች እንዲሁም የሌላ እምነት ተከታዮችም እንዲያወግዙት ጠይቋል፡፡


የአማራ ክልልም ተመሳሳይ በሙስሊሙ ላይ የሚደርሱ ተደጋጋሚ መዋቅራዊ ጥቃቶችን በማስቆም፣ አጥፊዎችንም እንዲቀጣ አሳስቧል፡፡ የክልሉ ምክር ቤቱ በዚሁ መግለጫ ላይ በዚህ ሦስት ዓመት መንግስት አጥፊዎችን በሕግ እንደማይቀጣ ማየቱን በመግለጽ፣ በሕዝብ ግብር የሚተዳደረው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም የሚላክለትን መግለጫ በተደጋጋሚ ሽፋን ባለመስጠት የጥፋተኞች ተባባሪ ሆኗል ሲል ከሷል፡፡


ኮርፖሬሽኑ በትላንትናው እለት የደረሰውን ድርጊትም መጠነኛ የፀጥታ ችግር በሚል ሸፋፍኗል ሲል ቅሬታውን ገልጧል፡፡


ትላንት ሚያዚያ ማክሰኞ ቀን 18፣ 2014 በጎንደር ከተማ ሸይኽ ከማል ለጋሥ የተባሉ የአገር ሽማግሌ ቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ የነበሩ የጎንደር ከተማ ሙስሊም ማኅበረሰብ አባላት ላይ በተከፈተ ድንገተኛ ጥቃት እስከአሁን የ21 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img