Sunday, May 19, 2024
spot_img

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ለብቻዬ ተነጥያለሁ ማለቱን ሕጋዊ አይደለም አሉ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ የካቲት 11 2014 የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ሐጂ ሡልጣን አማን የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከዋናው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለብቻዬ ተነጥዬ ራሴን ችያለሁ ማለቱን ሕጋዊ አይደለም ብለዋል፡፡

የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባቶች በተያዘው ሳምንት ትግራይ ውስጥ ብዙ ኢማሞች ሲገደሉ፣ ብዙ መስጅድ ሲፈርስ የፌዴራል እስልምና ጉዳይ ያደረገልን ነገር የለም በሚል ራሳቸውን ችለው መነጠላቸውን ገልጸው ነበር፡፡  

ነገር ግን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ለአሜሪካ ድምጽ የፌዴራል እስልምና ጉዳዮች ከኛ ጎን አልቆመም የሚለውን ክስ ተቋውመውታል፡፡ እኛ እንደ አዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮችም ሆነ ሌላው ድምጻቸውን አሰምቷል ብለዋል፡፡ በማሳያነትም ነጃሺ የተመታ ጊዜ ማንም ቢያደርገው ትክክል አይደለም ብለናል ያሉት ሐጂ ሡልጣን፣ በክልሉ ያለው የጦርነት ሁኔታ እንደሚታወቅ ጠቅሰው እርዳታ ለማድረስ መንገድም እንደሌላ ገልጸዋል፡፡ መንገድ ቢከፈት ለመርዳት ሁሉም ዝግጁ መሆኑንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡

ሐጂ ሡልጣን ሐጂ አማን የግላቸው መሆኑን ገልፀው በሰጡት አስተያየት ‹‹አሁን በጦርነቱ ምክኒያት መገናኘት አልተቻለም፤ ጦርነቱ ቆሞ ሰላም ሰፍኖ መገናኘት ሲቻል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የማስተካከል ኃላፊነት አለበት። እስከዚያ እኔ በግሌ ሕጋዊ ናቸው ብዬ አላምንም›› ብለዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኡለማ ምክር ቤት አባልና የሰላምና ሕግ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሐመድ ሲራጅ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የራሱን ምክር ቤት ማቋቋሙን በተመለከተ ላሳለፈው ውሳኔ ምላሽ ሰጥተዋል።

 ‹‹ትግራይና እኛ አንድ አገር እንጂ ሁለት አገር መሆናችንን ስለማናውቅ ምንም የማውቀው ነገር የለም፣ እንዲህ ያስባላቸውም ምን እንደሆነ አልተረዳሁም ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፌዴራል መጅሊስ መነጠሉን በገለጸበት ወቅት የፌዴራሉ መጅሊስ የገንዘብ ድጋፍ ካደረገልን አራት አራት ዓመት አስቆጥሯል ሲል ቅሬታ አቅርቦ ነበር፡፡ ለዚህ ጉዳይ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኡለማ ምክር ቤት አባልና የሰላምና ሕግ ዘርፍ ኃላፊው የእስልምና ጉዳዮች የሚያወጣቸው ወጪዎች ከሐጅ እና ዑምራ የሚገኝ እንደነበር ጠቅሰው፣ ሐጅ በኮቪድ የተነሳ ከቆመ ሦስት ዓመቱ ነው፡፡ መተዳደሪያ ገቢ በአካባቢው እንዳለ ነው የማውቀው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img