Sunday, May 19, 2024
spot_img

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት በክልሉ መስጂዶችና ምዕመኑ ላይ የሚደርሱ ትንኮሳዎችና ጥቃቶች ተባብሰዋል አለ

  • አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ም/ቤቱ የላከለትን መግለጫ ለማሰራጨት ፍቃደኛ አልሆነም


አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥር 18፣ 2014 ― የአማራ ክልል የእስልምና  ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በክልሉ መስጂዶችና ምዕመኑ ላይ የሚደርሱ ትንኮሳዎችና ጥቃቶች ተባብሰዋል ሲል ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ምክር ቤቱ ባሰራጨው መግለጫ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይ በደቡብ ጎንደር እና በምሥራቅ ጎጃም በተደራጀና በተቀነባበረ መንገድ በጠራራ ፀሐይ 7 መስጂዶችና በውስጡ የሚገኙ ቅዱስ ቁርኣን እና ሌሎች መጻሕፍት ‹‹በሃይማኖት ሽፋን እኩይ አላማቸውን ለማሳካት›› በሚንቀሳቀሱ ባላቸው አካላት መቃጠላቸውን አስታውሷል፡፡

ይህ ሁሉ ወንጀል በሕዝብ እና በአምልኮ ቦታዎች ላይ ሲፈጸም አንድም ወንጀለኛ ለሕግ ቀርቦ ውሳኔ እንዳልተሰጠው ያመለከተው ምክር ቤቱ፣ በዐል በመጣ ቁጥር የጎንደር ከተማን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች ስጋቱና ትንኮሳው መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡

ምክር ቤቱ ለዚህ በማሳያነት ከቀናት በፊት በተከበረው የጥምቀት በዐል ወቅት ተፈጽመዋል ያላቸውን ‹‹ሕዝብን ለግጭት የሚዳርጉ›› እና ‹‹የቆሰለች›› ያላትን ኢትዮጵያን ሰላሟን የሚያናጋ ያላቸውን ተግባራት ዘርዝሯል፡፡

ከነዚህ መካከል የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የግንብ አጥር መፍረሱን፣ በተመሳሳይ ባህር ዳር ከተማ አባይ ማዶ የሚኖሩት ትልቅ የሙስሊም አባት መኖሪያ ቤት በድንጋይ መደብደቡን፣ በደሴ ከተማ የአረብ ገንዳ መስጅድ ሙስሊሞች በስግደት ላይ ባሉበት ወቅት መስጂዱ በጥይት መደብደቡን፣ በጎንደር የሚገኘው ነስረላህ የተሰኘ መስጅድ አጥር እና ጣሪያ በጥይት መመታቱን እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም በሙስሊም መቃብር ላይ መስቀል የመትከል ድርጊት መታየቱንም ጠቅሷል፡፡   

እነዚህን አና ሌሎችንም ድርጊቶች ያወገዘው የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ፣ በተለይ በባህር ዳር የምክር ቤቱ አጥር ግንብ ሲፈርስ ስምሪት የተሰጣቸው የፖሊስ እና ሚሊሻ አባላት በዝምታ በመመልከታቸው እንዲጠየቁ ያለ ሲሆን፣ የክልሉ መንግስትና በየደረጃው ያለው አስተዳዳርም አደጋውን አርቆ በማሰብ ወንጀለኞች በሕግ አግባብ እንዲታረሙ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የአማራ ክልል የእስልምና ከፍተኛ ምክር ቤት ይህ መግለጫ ሳይቆራረጥ እንዲተላለፍለት የተላከለት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መግለጫውን ለማሠራጨት ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ ተነግሯል፡፡ ኮርፖሬሽኑ መግለጫውን ላለማስተላለፉ ያቀረበው ምክንያት ስለመኖሩ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡  

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img