Saturday, May 4, 2024
spot_img

ፈረንሳይ የኢትዮጵያ የብድር ጫና የሚቃለልበትን ሂደት ለማፋጠን ቁርጠኛ መሆኗ ተገለጸ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ የካቲት 1 2015 – በበለጸጉት 20 ሀገራት ማእቀፍ መሠረት ፈረንሳይ የኢትዮጵያ የብድር ጫና የሚቃለልበትን ሂደት ለማፋጠን ቁርጠኛ መሆኗን ከአገሪቱ ግምጃ ቤት የበላይ ኃላፊ ጋር መግለጻቸውን የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 1፣ 2015 እንዳስታወቀው፤ ሚኒስትር ዲኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶር) ከፈረንሳይ መንግስት ግምጃ ቤት የበላይ ኃላፊ ኢማኑኤል ሞሊን ጋር ‹‹በሁለቱ ሀገሮች ኢኮኖሚዊ ትብብር ላይ›› ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ኢዮብ በኢትዮጵያ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ የማህበረሰቦችን ክፍሎችን መልሶ የማቋቋሙ ሂደቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተው አስረድተዋል፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴር በዚህ የብሔራዊ ባንክ አዲሱ ገዥ ማሞ ምሕረቱን ባሳተፈው ውይይት፤ ፈረንሳይ በበለጸጉት 20 ሀገራት ማእቀፍ መሠረት የኢትዮጵያ የብድር ጫና የሚቃለልበትን ሂደት ለማፋጠን ፈረንሳይ ቁርጠኛ መሆኗ ተመላክቷል ብሏል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታው ኢዮብ ተካልኝ እና የፈረንሳይ መንግስት ግምጃ ቤት የበላይ ኃላፊ ኢማኑኤል ሞሊን ውይይት የተካሄደው፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ፈረንሳይ ተጉዘው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ከተገናኙ በኋላ ነው፡፡

ዐቢይ እና ማክሮን ትላንት ምሽት በነበራቸው ውይይት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ስለተደረገው የሠላም ስምምነት አፈጻጸምና ክትትል ላይ እንደሚያተኩሩ ቀድመው የወጡ መረጃዎች አመልክተው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለይም ባህልና ቅርስ መስክ ዋና ዋና ጉዳዮች ይሆናሉ ተብሎም ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img