Saturday, November 23, 2024
spot_img

የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን የሚደነግግ አዲስ መመርያ ተዘጋጀ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ኅዳር 26፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን በአግባቡ ለማካሄድ ያስችለናል ያለውንና አዳዲስ አሠራሮች የተካተቱበትን አዲስ መመርያ አውጥቷል።

ባንኩ አዲስ ባወጣው የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም፣ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሲፈቅዱ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለየትኞቹ ዘርፎች እንደሆነ በደረጃ በመከፋፈል ያስቀመጠበት ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ቅድሚያ ይሰጣቸው ያልነበሩ ምርቶች አሁን ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑን ያመላከተ ነው፡፡

ባንኮች ካላቸው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 50 በመቶውን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች መፍቀድ እንደሚኖርባቸው የሚጠቅሰው የመመርያው ክፍል፣ ከዚህ ቀደም ያልነበረ መሆኑንና በአዲሱ መመርያ እንዲካተት የተደረገ ስለመሆኑ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

በአዲሱ መመርያ የተካተተው ሌላው አሠራር ደግሞ፣ ባንኮቹ ያልተጠቀሙበትን የውጭ ምንዛሪ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረግ ያለባቸው መሆኑን መደንገጉ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ የባንክ ሥራ አስፈጻሚዎች አስቸኳይ ለሚባል በተለይ እንደ መለዋወጫ ዕቃ ላሉ ምርቶች በቀጥታ የውጭ ምንዛሪ መፍቀድ የሚችሉ መሆኑ በመመርያው መቀመጡ አዲስ ነገር ነው ተብሏል፡፡

የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ሪዘርቭ አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑት የኔሐሳብ ታደሰ ለጋዜጣው እንደገለጹት፣ አዲሱ መመርያ ለባንኮች እንቅፋት የሆኑ አሠራሮችን የሚያስወግድ ሲሆን፣ ቅድሚያ ላልነበራቸው ዘርፎች የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡

ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብሎ ካስቀመጣቸው ዘርፎች ውስጥ በመጀመርያው ረድፍ የተቀመጡት የፋርማቲውካል ግብዓቶችን፣ የምግብ ዘይት ግብዓቶችና ነዳጅን ነው፡፡ ይህም በተለይም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ከአቅማቸው በታች ሲሠሩ ለነበሩ የዘይት ፋብሪካዎች ዕፎይታ ይሰጣል ተብሏል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የውጭ ምንዛሪ ሊፈቀድላቸው ይገባል ተብሎ በመመርያው የተጠቀሱት ደግሞ የግብርና ግብዓቶች የሆኑትን ማዳበሪያ፣ ዘር፣ የአረም መድኃኒቶችና ኬሚካሎችን ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወደ 15 የሚሆኑ ዘርፎች የተከፋፈሉ ምርቶች ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በቀዳሚነት የውጭ ምንዛሪ ሊሰጣቸው ይገባል ተብሎ በመመርያው የተቀመጠው የሞተር ዘይት፣ የሞተር ቅባቶችና የግብርና የማሽነሪዎች ናቸው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

2 COMMENTS

  1. እንደዚህ አይነት ማሻሻያዎች ለሀገራችን ህዝብ ህይወት መቀየር መሰረት ስለሆነ በጣም ጥሩ ማሻሻያ ነው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img