Monday, November 25, 2024
spot_img

በኢትዮጵያ የመጀመርያው የግል ሞርጌጅ ባንክ በዛሬው እለት ሥራ ጀመረ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 15 2014 ― በዋናነት የቤት ፋይናንስ (ሞርጌጅ) አገልግሎት ለማቅረብ አልሞ የተመሠረተው ጎህ ቤቶች ባንክ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 15፣ 2014 በተከናወነ ሥነ ሥርዐት የመጀመሪያ ቅርንጫፉን በመክፈት ሥራ ጀምሯል፡፡

በባንክ ዘርፍ የካበተ ልምድ ባላቸው ባለሞያዎች እና ታዋቂ ባለሐብቶች እንደተቋቋመ የተነገረለት ጎህ ቤቶች በዋናነት የቤት ብድር ለማቅረብ አቅዶ የተመሰረተ መሆኑን የካፒታል ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በቀጣዮቹ ጊዜያት ተጨማሪ ቅርንጫፎችን እንደሚከፍት ያስታወቀው ባንኩ፣ የመጀመሪያ ቅርንጫፉን በአፍሪካ ጎዳና፣ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ ከፍቶ ስራ አስጀምሯል፡፡

ጎሕ ቤቶች ባንክ በ1 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር የተፈረመ እንዲሁም በ521 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በአስራ አንድ የባንክ ከፍተኛ ባለሞያዎች እና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ ነው። ከመስራቾቹ መካከል የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ እና የልማት ባንክ ፕሬዝደንት የነበሩት አቶ ጌታሁን ናና፣ የእናት ባንክ ፕሬዝዳንት የነበሩት ወይዘሮ ፋሲካ ከበደ፣ የጊፍት ሪል ስቴት መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብረኢየሱስ ኢጋታ ይገኙበታል።

ባንኩ ዛሬ ሥራ ሲጀምር አንድ ቢሊዮን ብር ለመኖሪያ ቤት ፈላጊ ደንበኞቹ በብድር ለማቅረብ ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን፣ አቅሙ ሲዳብር በቤቶች ግንባታ ዘርፍ የመሰማራት ሐሳብ ጭምር አለኝ ብሏል።

ጎሕ ቤቶች ባንክ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች የሚገዙበት የረዥም ጊዜ ብድር ያቀርባል የተባለ ሲሆን፣ የባንኩ ደንበኛ የተበደረውን ገንዘብ እስከ 30 ዓመት በሚደርስ ጊዜ ከነ ወለዱ ከፍሎ እንደሚጨርስ ባንኩ አስታውቋል፡፡

ከጎሕ በተጨማሪ ሠላም የተባለ ባንክ በተመሳሳይ ዘርፍ ላይ ትኩረቱን በማድረግ ገበያውን ለመቀላቀል በምሥረታ ላይ ይገኛል። ይህ ባንክ የታዋቂው ጫማ አምራች ሶልሬቤልስ ባለቤት ቤተልሔም ጥላሁን እና የምጣኔ ሐብት ባለሞያውና ፌርፋክስ አፍሪካ ግሎባል ሊቀመንበር የሆኑት ዘመዴነህ ንጋቱን ጨምሮ በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በሚያደርጉ ግለሰቦች በምሥረታ ላይ የሚገኝ ነው። ሠላም ባንክ በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ለ100 ሺሕ የመኖሪያ ቤቶች 200 ቢሊዮን ብር ብድር የማቅረብ ዕቅድ እንዳለው ይናገራል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img