Saturday, September 21, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ ብድር የመመለስ አቅም ደረጃው ዝቅ ተደረገ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 11 2014 ― የኢትዮጵያ ብድር የመመለስ አቅም ደረጃ ዝቅ ያደረገው ሙዲስ የተባለው ዓለም አቀፋዊ በሆኑ በተለያዩ የፋይናንስና ምጣኔ ሐብት እንዲሁም የብድር ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን በማድረግ የሚታወቅ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ ባወጣው ደረጃ የኢትዮጵያን ደረጃ ቀድሞ ከነበረው ቢ2 ወደ Caa2 ዝቅ አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ገደማ ተቋሙ ይፋ ባደረገው ደረጃ፣ በወቅቱ ያራዘመችው ብሔራዊ ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረው አለመግባባት በቀጣይ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በመጠቆም ከነበራት የቢ1 ደረጃ ዝቅ አድርጓት ነበር፡፡

አሁን በወጣው ደረጃ ሙዲስ ደረጃውን ዝቅ ለማድረጉ ያስቀመጠው ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ማስተካከያ ማድረጓ እንዲሁም ተባብሶ ቀጥሏል ያለውን ጦርነት ነው፡፡

ሙዲስ በዓለም ላይ ካሉ ከሦስቱ ተሰሚነት ካላቸው ተመሳሳይ ተቋማት አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ሲሆን፣ አገራትና መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች ሙዲስን የመሳሰሉ የምጣኔ ሀብትና የፋይናንስ ተቋማት በሚያወጧቸው ትንተናዎችና ደረጃዎች ላይ በመመርኮዝ ቁልፍ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ።

ከዚሁ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጋር በተገናኘ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ኢትዮጵያ ከቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት 2022 አስከ 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚኖራትን አጠቃላይ አገራዊ ምርት እድገትን (ጂዲፒ) መተንበይ እንዳልቻለ በቅርቡ አሳውቋል፡፡ ድርጅቱ ለዚህ እንደ ምክንያት ያስቀመጠው በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ ‹‹ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ እርግጠኛ ያለመሆን›› በመኖሩ እንደሆነ ገልጿል።

ይህ የድርጅቱ አስተያየት የመጣው በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ አንድ ዓመት ሊደፍን ያለውን ግጭት ተከትሎ ነው። አይኤምኤፍ የዓለም ምጣኔ ሀብት ገጽታ ባሳየበት ሪፖርቱ ላይ በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት የኢትዮጵያ አጠቃላይ አገራዊ ምርት 2 በመቶ እድገት ያሳያል ሲል የተነበየ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ከነበረው በአራት በመቶ ዝቅ ያለ ነው ብሏል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img