አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ታኅሣሥ 19፣ 2015 ― በኢትዮጵያ የሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት በመጀመር ቀዳሚ የሆነው ዘምዘም ባንክ፣ በመጀመርያው የሥራ ዘመኑ ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ደግሞ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገልጧል፡፡
ባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጸጸሙን በተመለከተ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ በሒሳብ ዓመቱ 146 ሚሊዮን ብር ኪሣራ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህ የተመዘገበው ኪሣራ ተጠባቂ መሆኑን አመልክቷል፡፡
እንደ ባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት፣ ከወለድ ነፃ ባንክ ከባህሪው አንፃር ፋይናንስ ያደረገው (ያበደረው) ገንዘብ ትርፍ በአንድ ጊዜ የሚገኝበት ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የተመዘገበ ኪሣራ እንጂ፣ ፋይናንስ እያደረገ ካለው ኢንቨስትመንቱ ትርፍ እያስመዘገበ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ በሥራ መጀመርያው ዓመት ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱም ኪሣራ ለማጻፉ አንድ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ፋይናንስ የተደረገው የገንዘብ መጠን ከ680 ሚሊዮን ብር ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ለፋይናንስ የሚያውለው ተጨማሪ አቅም እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡
ከ15 ዓመታት በፊት ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ የሚፈቅደው ሕግ ከወጣ ወዲህ አሥራ አንድ ባንኮች አገልግሎቱን መስጠት ጀምረዋል፡፡ አሥራ አንዱ ባንኮችና ሁለቱ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙት ባንኮች በድምሩ ከ170 ቢሊዮን ብር በላይ ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ የሰባሰቡ ሲሆን፣ ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከወለድ ነፃ አስቀማጭ ደንበኞችን ማፍራት ችለዋል፡፡