አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ታኅሣሥ 19፣ 2015 ― የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ቫይረስ በአገር አቀፍ ደረጃ መከሰቱን ተከትሎ ላለፉት ሦስት ዓመታት ለቫይረሱ ምላሽ እና በመደበኛ አገልግሎት ያገለገሉ 436 የጤና ባለሞያዎች ኮንትራት ያቋረጠው ‹‹ወረርሽኙ ትርጉም ባለው ደረጃ መቀነስ ጋር ተያይዞ በዚህ ወረርሽኝ ዙሪያ የነበረው የአጋር ድርጅቶች የበጀት ድጋፍም ስለቆመ›› መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ስለ ጉዳዩ በሰጠው መግለጫ፤ የኮቪድ 19 ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በፌዴራል እና በክልሎች ደረጃ ከ5912 በላይ የተለያየ ሞያ ያላቸው የጤና ባለሙያዎችን እንደ ሁኔታው በየስድስት ወሩ ሊታደስ በሚችል የኮንትራት ቅጥር በመቅጠር ማሰማራት መቻሉን አስታውሷል፡፡
እነዚህን በኮንትራት ተቀጥረው በሥራ ላይ የነበሩ ባለሞያዎችን በመጀመሪያ ለስድስት ወር ቢቀጠሩም ኮንትራታቸውን በተከታታይ ማደሱን የገለጸው የጤና ሚኒስቴር፤ የወረርሽኙ ሁኔታ ቢቀንስም ‹‹ከማገልገላቸዉ አንጻር እና በየተቋማቱም መስራት ቢቀጥሉ በአብዛኛዉ ለአገልግሎቱ ስለሚያስፈልጉ›› ወደ ቋሚነት በማዘዋወር ለማሰራት እንዲቻል ከፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ በጀትና ክፍት ቦታ እስካለ ድረስ በልዩ ሁኔታ ማስታወቂያ ማውጣት ሳያስፈልግ የሚቀጠሩበትን እድል ለማመቻቸት ሞክሬያለሁ ብሏል፡፡
በዚህ መሠረት በኮንትራት ከተቀጠሩት ውስጥ በፌደራል እና በሁሉም ክልሎች በተደረገው ቅጥር 5101 ባለሞያዎች እንደ ሀገር ወደ ቋሚነት ማሸጋገር ተችሏል ያለው መግለጫው፤ ቀሪዎቹን 436 ባለሙያዎች ግን ኮንትራታቸውን ለማቋረጥ ተገድጃለሁ ነው ያለው፡፡
ሚኒስቴሩ እነዚህ ኮንታራታቸው የተቋረጠባቸው ባለሞያዎች በተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ተቋማት ባሉ ክፍት መደብ አመልክተው የመቀጠር ዕድል እንዳላቸው የገለጸ ሲሆን፣ በተለይ ሐኪሞችን አስመልክቶ ‹‹በማቺንግ ፈንድ የተመቻቸ የስራ እድል›› በክልሎች ደረጃ ስላለ፤ እድሉን በቀላሉ መጠቀም እንደሚያስችላቸውና ሌሎች ባለሞያዎችም ቢሆኑ ወደ ክልል በመሄድ ባሉት የስራ እድሎች መቀጠር የሚችሉ መሆናቸውና ‹‹በወሳኝ ሰዓት ያገለገሉበት እና ያካበቱት ልምድ›› በውድድር ጊዜ ታሳቢ የሚደረግ መሆኑን ጠቁሟል፡፡