Saturday, May 18, 2024
spot_img

የፖሊስ ሥያሜና የማዕረግ መጠሪያዎች እንዲቀየሩ ጥናት መቅረቡ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሚያዝያ 29፣ 2013 ― በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አጠቃላይ የማሻሻያ ሥራ ላይ እየተከናወኑ ያሉ የጥናት ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኘው የሰላም ሚኒስቴር ባስጠናው ጥናት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ‹‹የፌደራል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ›› የሚል ሥያሜ እንዲኖረው ሐሳብ መቅረቡ ተሰምቷል፡፡

በክልል ደረጃ የሚደራጁ የፖሊስ ኮሚሽኖች ደግሞ አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው በየክልሉ ሥያሜ በጠቅላይ መመሪያ ደረጃ እንዲደራጁ ታስቧል ነወ የተባለው፡፡

በዚህ መሠረት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ወደ አማራ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ሥያሜያቸው እንዲቀየር ሌሎችም የክልል ፖሊስ ኮሚሽን አደረጃጀት በዚህ መልኩ እንዲደራጅ የሚያደርግ ጥናት መቅረቡን ዋዜማ ራድዮ ዘግቧል፡፡

በጥናቱ ላይ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና በክልሎች የፖሊስ ኮሚሽኖች መካከል ያለው የተጠሪነት የተዋረድ ሥልጣን ኃላፊነት በሀገሪቱ እየተስተዋሉ ላሉ የፀጥታ መደፍረስ እና ሕግን የማስከበር እንቅስቃሴ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ እንደ መሰረታዊ ችግር ቀርቧል።

በሰላም ሚኒስቴር በኩል ተዘጋጅቶ ለውይይት ሊቀርብ በተሰናዳው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዶክትሪን ላይ እንደሰፈረው ‹‹የፖሊስ ተልዕኮ በዋነኛነት ከዜጎች ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጋር እጅግ የተቆራኘ በመሆኑ ከሁሉ በፊት ውስጣዊና ውጫዊ የአደረጃጀት ሥርአቱ በግልፅ አሰራርና ፍልስፍና መገንባት አለበት›› ይላል።

አስከትሎም በገፅ 23 “የፖሊስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በግልፅ የአደረጃጀት ስርዓት ካልተደራጁ የስራ ወይም የኃላፊነት ግጭት እና የፍላጎት ወይም የጥቅሞች ግጭት በመፍጠር የተሰጣቸውን ተልዕኮ እና የተቋቋሙበትን አላማ በመሳት ላልተፈለገ ግጭትና መስዋዕትነት ይዳረጋሉ›› ሲል ደምድሟል።

የፌደራል እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽን አደረጃጀት እስከዛሬ በኮሚሽን የአደረጃጀት መጠሪያ በተመሳሳይ ቅርፅ መደራጀታቸው መመሪያዎችን እና ተልእኮዎችን በመቀበል ደረጃ ችግር ሆኖ መቆየቱንም ነው ይህ የውይይት ሰነዱ እንደያወሳ በዘገባው ተመላክቷል፡፡

የፖሊስ አደረጃጀት ፍልስፍና የፌዴራል ስርዓቱን ቅርፅ እንደሚከተል ይገልፅና ‘’በፌዴራል ደረጃ የሚኖር የፖሊስ አደረጃጀት የሚኖረው ስልጣን በዋነኛነት ለፌዴራል ፍ/ቤቶች የተሰጡ የስልጣን ወሰኖችን መሰረት የሚደርግ ሲሆን የክልል ፖሊስ ስልጣንም ምንጩ ለክልል ፍ/ቤቶች በተሰጡ ስልጣን ወሰኖች ውስጥ ሆኖ ከየስራ ክፍሎቹ ለየት ያለ ባህርይና ተልዕኮ ጋር የተገናኘ ነው’’ ሲልም ይዘረዝራል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ከአስተዳደር ክልል ወሰን የተሻገረ የጋራ ወንጀልን የመቆጣጠር የተዋረድ የጋራ ስራ ብዙ መሳናክሎች የነበረበት በመሆኑም ይህን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ግልፅ አሰራር ማስቀመጥ መፍትሔ መሆኑንም ይጠቁማል።

የዚህ የተጠሪነት ወይም የስልጣን ተዋረድ አስፈላጊነት ክልሎች ባላቸው የፖሊስ ኮሚሽን አደረጃጀት ምክንያት ከማእከል ጋር ያለው አልያም ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደ ሀገር የጋራ ራእይ ሰንቆ ለጋራ የደህንነት መረጋገጥ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በክልሎች የመታጠር ውሱንነት በመስተዋሉ መሆኑን የሚያብራራው ጥናቱ ይህንን ችግር ለመፍታት ያለመ የአደረጃጀት ክለሳ ስለመሆኑም ይጠቁማል።

የፖሊስ የአደረጃጀት መዋቅሩን ‹‹ኮሚሽን›› ከሚለው ሥያሜ ወደ ‹‹ጠቅላይ መምሪያ›› ሥያሜ ለመቀየር አስፈላጊ ከሆኑ መነሻዎች መካከል ለፌደራልና ለክልል በህግ በተሰጡ ህገ መንግስታዊ ተልእኮዎች መነሻነት መሆኑን የሚያብራራው ይህ ሰነድ፣ ሌላው ዓቢይ ምከንያት ደግሞ ‘‹‹የፖሊስ አደረጃጀት አጠቃላይ ዓላማና ግብ ኢትዮጵያዊ የሆነ የፖሊስ ተቋምን በመገንባት ላይ ያተኮረ ሆኖ የአደረጃጀቱ ቅርፅና ይዘቱ የፌዴራል አወቃቀሩን የተከተለ ይሆናል›› ሲል ተቋሙንም ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዋህዶ ይበልጥ መልክ ማስያዝም እንደሚያስፈልግ ይገልጻል።

ከተቋሙ መጠሪያ ስም ለውጥ ባሻገር ከዚህ ቀደም በፖሊስ አገልግሎት ውስጥ ይሰጡ የነበሩ የማዕረግ መጠሪያዎች ጭምር ሀገራዊ ለማድረግም የሚያስችል ጥናት መቅረቡም ተሰምቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img