Saturday, May 18, 2024
spot_img

ተመራቂ የጤና ባለሞያዎች በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መዋጮ ደመወዝ ሊቀጠሩ መሆኑ ታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 25 2014 ― የጤና ሚኒስቴር፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ለጤና ባለሞያዎች የሚከፈልን የደመወዝ ወጪ እየተጋሩ፣ አዳዲስ ምሩቃን የጤና ባለሞያዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ በቅጥር ወደ ሥራ የሚያስገባበትን ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል፡፡

ሚኒስቴሩ፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ይህን አሠራር ለመተግበር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ፣ ታኅሳስ 21፣ 2014 የተፈራረሙ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ደረጃ ወጪውን ከሚጋራው የገንዘብ ሚኒስቴርና ለፕሮጀክቱ ትግበራ የገንዘብ ድጋፍ ካደረገው ‹‹በፌት›› የተሰኘ ፋውንዴሽን ጋር ተመሳሳይ ስምምነት መደረጉ ተገልጿል፡፡

እስከ 2011 መጨረሻ ድረስ የጤና ሚኒስቴር ተመራቂ የጤና ባለሞያዎችን በመቀበል፣ በመላ የአገሪቱ ክፍሎች ምደባ ያከናውን የነበረ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ ይህን አሠራር ካስቀረ በኋላ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የጤና ተቋማት ማስታወቂያ እያወጡ በራሳቸው እንዲቀጥሩ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡

ይሁንና በበጀት እጥረት ምክንያት አስተዳደርና ተቋማቱ የሚፈለገውን ያህል የጤና ባለሞያ መቅጠር እንዳልቻሉ ለሪፖርተር ጋዜጣ የተናገሩት የሚኒስቴሩ የሰው ሐብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሐብታሙ ደምሴ፣ ይህ ተመራቂ የጤና ባለሞያዎች እንዲጉላሉና ሥራ አጥ እንዲሆኑ እንዳደረገ አስረድተዋል፡፡ ተመራቂ የጤና ባለሞያዎችም በጤና ዘርፉ ላይ የባለሞያ እጥረት እያለ ሥራ አጥ መሆናቸውን በማማረር ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡

አሁን ሚኒስቴሩ ይፋ ያደረገው የወጪ መጋራት ፕሮጀክት፣ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ላይ የተጣለውን የደመወዝ ክፍያ ወጪ የፌዴራል መንግሥቱ እንዲጋራው በማድረግ፣ በበጀት እጥረት ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ያለመ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፣ የጤና ሚኒስቴር ከአጋር የልማት ድርጅቶች ሀብት ሲያሰባስብ የገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ የተሰበሰበውን ገንዘብ መጠን ያህል ያዋጣል፡፡

በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዓመት ላይ ጤና ሚኒስቴር ባገኘው ዕርዳታ አማካይነት፣ የጤና ባለሙያዎችን 50 በመቶ ደመወዝ ሲከፍል፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ቀሪውን ግማሽ ይሸፍናል፡፡ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች በመጀመሪያው ዓመት ላይ ያለባቸው ግዴታ የባለሙያዎችን ጥቅማ ጥቅም መክፈል ብቻ ይሆናል፡፡

በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ላይ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች በፕሮጀክቱ አማካይነት የሚቀጠሩ አዲስ የጤና ባለሙያዎች፣ ደመወዝ በየቅደም ተከተሉ 25 እና 50 በመቶ ይከፍላሉ፡፡ በአራተኛው ዓመት ላይ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ደወመዝ ወጪን በመክፈል ባለሙያዎቹን ቋሚ አድርገው ይቀጥላሉ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ይኼንን ፕሮጀክት በመተግበር የጤና ባለሙያዎችን የደመወዝ ወጪ ቀስ በቀስ ወደ ክልልና ከተማ አስተዳደሮች በማዞር፣ በአንድ ጊዜ ለመቅጠር በሚሞክሩ ጊዜ የሚያጋጥማቸውን ችግር የማቃለል ዕቅድ አለው፡፡ ምንም እንኳን ይኼ ፕሮጀክት ይፋ ቢደረግም አስተዳደሮቹ ከዚህ በፊት ሲያከናውኑት የነበረው መደበኛ ቅጥር ባለበት እንደሚቀጥል አቶ ሐብታሙ አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዚህ ዓመት 2 ሺሕ 900 ያህል ተመራቂ የጤና ባለሙያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ የያዘ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በሚቆይባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ ከስድስት ሺሕ በላይ ባለሙያዎች ይቀጠራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት አማካይነት የሚቀጠሩት የጤና ባለሞያዎች የእናቶችና ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ለወደሙ ተቋማት መልሶ ማቋቋም የሚመደቡ የጤና ባለሞያዎች እንደሚኖሩም ተጠቁሟል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img