Saturday, May 18, 2024
spot_img

በአፋር ክልል ከ60 በላይ የጤና ተቋማት በሕወሓት ኃይሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 2 2014 ― የሕወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ውስጥ በቆዩባቸው ጊዜያት ከ60 በላይ የጤና ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተነግሯል፡፡

ይህንኑ የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ እንደነገሩት ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

‹‹ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አንድ ሆስፒታል እና ወደ 62 የጤና ተቋማትም ወድመዋል›› ያሉት አቶ ያሲን፣ ጉዳት የደረሰው በ17 የጤና ጣቢያዎች፣ በአንድ ሆስፒታል እና በ42 የጤና ኬላዎች ላይ እንደሆነ እና ጉዳቱም የተቋሙ ግንባታ መሰባበር እና የመድኃኒት ዘረፋን እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ያለውን የጤና ሥርዓት ‹‹አንኮታኩተው ነው የሄዱት። የደረሰው ጉዳት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ይደርሳል›› ሲሉም አክለዋል።

የጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ እስከሚካሄድ ድረስ ተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድን በመላክ ለሕዝቡ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነም ኃላፊው አስረድተዋል።

‹‹ከዚህ በፊት ወደ 20 ቡድን ነበረን። አሁን ከ5 እስከ 10 የሚደርስ ተጨማሪ ተንቀሳቃሽና ጊዜያዊ እርዳታ ሰጪ ቡድን አሰማርተናል። ለመርዳት አስቸጋሪ የሆኑ አካባቢዎች ላይ አብዳ የሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት እየሠራ ነው›› ብለዋል።

እነዚህ ቡድኖች ክትባት መስጠት እና ማዋለድን ጨምሮ የመጀመሪያ ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል። በተለይም ወደ ጤና ጣቢያ ሪፈር በማድረግ እና ሰዎችን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ረገድ ሚናቸው የጎላ እንደሆነም አክለዋል።

ሆኖም ግን ይህ አገልግሎት መደበኛ የጤና ተቋም አገልግሎትን ሊተካ ስለማይችል ክፍተት እንደተፈጠረ ጠቁመዋል።

በተለይም ዞን 2 እና ዞን 4 እንዲሁም ዞን 5 በተባሉት አካባቢዎች የጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ብለዋል። ለረዥም ጊዜ ሕክምና ሳያገኙ የቆዩ የገጠር ነዋሪዎች አሁን ላይ የሕክምና ተቋማቱ አገልግሎት ይሰጣሉ ብለው አስበው ቢሄዱም ሕክምና ለመስጠት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

የአፋር የጤና ሥርዓትን ለማቋቋም እና መሣሪያ ለማሟላት ከ20 ዓመት በላይ እንደወሰደ በመጥቀስ፤ ‹‹ይህን ሁሉ ጊዜ ባለሙያ የለፋበት ነበር። አርብቶ አደሩም ወደ ጤና ተቋም እየመጣ በአግባቡ እየተጠቀመ ባለበት ሰዓት ነው ውድመቱ የደረሰው›› ብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img