Sunday, May 19, 2024
spot_img

የሕግ ባለሞያው ዐብዱልጀባር ሑሴን ሥርዓተ ቀብር ዛሬ በአዳማ ከተማ ተፈጸመ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 6፣ 2013 ― በትላንትናው እለት ሕይወታቸው ማለፉ የተሰማው የሕግ ባለሞያው የአቶ ዐብዱልጀባር ሑሴን የቀብር ሥነ ስርአት በዛሬው እለት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ከተማ ተፈጽሟል።

የአቶ ዐብዱልጀባር አስከሬን ዛሬ ረፋድ ላይ ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ ምኒልክ ሆስፒታል ተወስዶ ምርመራ የተደረገለት ሲሆን፣ የህልፈታቸውን ምክንያት በተመለከተ እስካሁን በይፋ ከሆስፒታሉ የተገለፀ ነገር የለም።

አዲስ ስታንዳርድ የቅርብ ጓደኛቸው መሐመድ ጂማ ነግረውኛል ብሎ እንደዘገበው ከሆነ አቶ ዐብዱልጀባር ሞተው የተገኙት በአዳማ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 12 ሲሆን፣ ሰዐቱም ምሽት ከ1 እስከ 30 ባለው ነው።

በአካላቸው ላይ ምንም ዐይነት የሚታይ ጉዳት እንዳልነበር የገለፀው መሐመድ፣ ቅድሚያ ወደ አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውንም ነው ያመለከተው።

በሌላ በኩል የአዳማ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ኃላፊ መኩሪያ ድንቁ በበኩላቸው ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡ ሰዎች ተናገሩ ብለው እንደገለጹት፣ ጠበቃው ሞተው ተገኝተዋል በተባለበት አካባቢ ቀድሞ ሰዎች ወደ ባለቤታቸው እንዲደውሉ ስልኳን እንደሰጡና ባለቤትየው ስኳር ወይም ከረሜላ ስጡት ማለቷንና በዚህም የጤናቸው ሁኔታ በጥቂቱ መሻሻሉን አመልክተዋል።

አክለውም ሌላ ጊዜ ጠበቃው ሕመም ሲያገኛቸው ወደ ሆስፒታል የሚወስዳቸው ባጃጅ ወደ ሪፍት ቫሊ ሆስፒታል ሊወስዳቸው ቢመጣም ወደ አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል እየተወሰዱ ባሉበት ሕይወታቸው ማለፉን የፖሊስን ምርመራ ጠቅሰው አመልክተዋል።

ኃላፊው በሌላ በኩል አቶ ዐብዱልጀባር ሕይወታቸው ያለፈው በሪፍት ቫሊ ሆስፒታል ነው የሚሉ መረጃዎች ቢኖሩም ከድምዳሜ ላይ አለመድረሳቸውን የገለፁ ሲሆን፣ የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ባለሞያዎች ምንም ዐይነት ጉዳይ እንዳልደረሰባቸው መግለጻቸውም ተመላክቷል።

የአቶ ዐብዱልጀባር የቅር ጓደኛ የሆነው መሐመድ ጂማም ይህንኑ የሚያጠናክር መረጃ ሰጥቷል።

እንደ መሐመድ ከሆነ ጠበቃው ራሳቸውን ስተው ያገኟቸው ሰዎች ወደ ባለቤታቸው መደወላቸውንና እርሷ መንገድ ላይ ስለነበረች ስኳር ስጡት እንዳለችና ስትደርስ ወደ ሪፍት ቫሊ ሆስፒታል እንደወሰደቻቸው እንዲሁም ወደ እርሳቸው ጋር ደውላ እዚያው እንገናኝ ብላዋለች።

መሐመድ ባለቤቱ ነገረችኝ ብሎ ሲናገር እርሷ ጠበቃው ራሳቸውን ስተው ከወደቁበት ሥፍራ ስትደርስ የእጅ ስልካቸው በኪሳቸው እንዳልነበርና ያገኗቸው ሰዎች በሌላ ቁጥር ነው የደወሉት።

መሐመድ ጓደኛው የሞቱበትን ሰአት በትክክል መናገር ቢከብድም ባለቤታቸው ወደ ሆስፒታል ስትወስዳቸው መሞታቸውን ገልጿል።

የጠበቃውን ሞት በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር መድረኮች የተለያዩ መረጃዎች እየተሰራጩ የሚገኝ ሲሆን፣ ከጠበቃው ጋር በኦሮሞ ፖለቲከኛ እስረኞች ቡድን ውስጥ ተከላካይ ጠበቃ የሆኑት ግርማ ጉተማ የፖሊስን የምርመራ ውጤት እየጠበቅን ነው ማለታቸውን አዲስ ስታንዳርድ አስነብቧል።

አዲስ ዘይቤ በበኩሉ ከአቶ ዐብዱልጀባር ቀብር ሥነ ስርአቱ በኋላ ወጣቶች “የሞተበት ምክንያት ይገለፅልን” እንዲሁም “እነጃዋር ዛሬ በድጋሚ ታሰሩ” የሚሉ ድምጾችን ማሰማታቸውን አስነብቧል።

አቶ ዐብዱልጀባር ሑሴን ባለትዳር እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበሩ።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img