አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ ሰኔ 17፣ 2014 ― የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምሩባት ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2022 ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከተመዘገበባቸው የአፍሪካ ቀዳሚ ሦስት አገራት መካከል ተካታለች፡፡
አፍሪካን ቢዝነስ ኢንሳይደር ይዞት የወጣው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከተመዘገበባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡
እንደ መረጃው በአህጉሩ ከፍተኛውን የዋጋ ግሽበት ያስመዘገበችው፤ ያለፉትን ዓመታት ፖለቲካዊ መረጋጋት የራቃት የኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን ሆናለች፡፡ በሱዳን የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 245.1 በመቶ ሲሆን፣ በደቡባዊ ምሥራቅ የአፍሪካ ክፍል የምትገኘው ዚምባቡዌ 86.7 በመቶ የዋጋ ግሽበት ተመዝግቦባት ሁለተኛዋ አገር ሆናለች፡፡ በኢትዮጵያ የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 34.5 በመቶ ሆኗል፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት በአገሪቱ በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ መሆኑን ባለፈው ወር ገልጧል፡፡ ምክር ቤቱ የዘጠኝ ወራት የምጣኔ ሀብት አፈጻጸምን ገምግሞ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ ፈተና እየገጠመው ያለው ከዋጋ ግሽበት አንጻር መሆኑን ጠቁሞ ነበር፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ከሳምንታት በፊት ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አላቸው ከሚባሉ ዐሥር የዓለም አገራት ዘጠነኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል፡፡
ማኅበሩ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት፣ በዋጋ ግሽበት እና ችግሮች ዙሪያ ለስድስት ወራት ያደረገውን ጥናት በወቅቱ ይፋ ሲያደርግ የዋጋ ግሽበት የኢትዮጵያ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል ብሏል። የተፈጠረው የኑሮ ውድነት የኅብረተሰቡን ኅልውና እየተፈታተነ ይገኛል ሲልም አክሎ ነበር፡፡
በዓለም ገንዘብ ድርጅት መረጃ ከሱዳን፣ ዙምባቡዌ እና ኢትዮጵያ ውጪ ከአፍሪካ አንጎላ፣ ሴራሊዮን፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዛምቢያ እንዲሁም ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ እስከ አስረኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡