Tuesday, May 7, 2024
spot_img

ኢሰመኮ በምሥራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት ለማስከበር በቂ የፀጥታ ኃይሎች በቋሚነት ሊሰማሩ ይገባል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 8፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) በምሥራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በመስፋፋት ላይ በመሆናቸውና ባሕሪያቸውን እየቀየሩ ብሔር ተኮር ወደ ሆነ የእርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ የሚችል በመሆኑ፣ መንግስት በቂ የፀጥታ ኃይሎችን በአፋጣኝና በቋሚነት በአካባቢው ሊያሰማራ እንደሚገባ አሳስቧል።

ጊዳ ኪራሙ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ የምስራቅ ወለጋ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአስጊ ሁኔታ እንደሚገኙ በመግለጽ፣ ወደ ወረዳው የሚወስዱ የተዘጉ መንገዶችን ማስከፈትን ጨምሮ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራሉ ኃይሎች ጋር ሊቀናጁ እንደሚገባ ማሳሰቡን ያስታወሰው ኮሚሽኑ፣ ይሁንና ሀሮ ከተማ ላይ የነበረው “የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ለሌላ ስራ አካባቢውን ለቅቆ መውጣቱን” ተከትሎ፣ በሀሮ አዲስ አለም ቀበሌ ከመስከረም 30፣ 2014 ጀምሮ ሲቪል ሰዎች “በኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ነግረውኛል ብሏል።

በዚሁ ከተማ ይህንኑ ግድያ ምክንያት በማድረግ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት የተደራጁ የተወሰኑ የአካባቢው እና አጎራባች ክልል ነዋሪዎች በሲቪል ሰዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የተጎጂዎች ቤተሰቦችና  የአካባቢው አስተዳደር  አካላት መረዳት መቻሉንም ገልጿል።

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በኡሙሩ ወረዳ ደግሞ ከነሃሴ 12፣ 2013 ጀምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች በሆኑና “ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ” በሚል መሳሪያ እንዲታጠቁ ስለመደረጋቸው ወይም እንደተፈቀደላቸው በሚነገር የአካባቢው ነዋሪዎቸ በተፈጸሙ ጥቃቶች በተመሳሳይ በርካታ ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉም ኢሰመኮ አሳውቋል። እነዚህ ሁሉ ጥቃቶችና ግድያዎች የብሔር ማንነትን መሰረት አድርገው አንድ ጊዜ በአማራ ብሔር ተወላጆች፣ ሌላ ጊዜ በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ብሔር ተኮር ጥቃቶች በመሆናቸው፣ በአካባቢው ነዋሪዎች በሆኑ በሁለቱ ብሔር ተወላጆች መካከል ከፍተኛ ውጥረትና የእርስ በእርስ ግጭት ስጋትን ፈጥሯል ነው ያለ።

ይህንኑ ግጭት በመሸሽ ከምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ፣ ጉደያ ቢላ ወረዳ፣ ኪረሙ ወረዳ፣ ሌቃ ዱለቻ ወረዳ፣ በዲጋ ወረዳ፣ እና ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በአጠቃላይ 43 ሺሕ 139 በላይ ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ የዞኑ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላትን ጠቅሶ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ወደ እነዚህ አከባቢዎች የሚያደርሱ መንገዶች አሁንም ዝግ በመሆናቸውና በአከባቢው ያለው ውጥረት አሁንም ባለመርገቡ ምክንያት ሰዎች መሰረታዊ አቅርቦቶችንና ሕክምና ለማግኘት ጭምር በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙም አመልክቷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ በተለይም የአካባቢውንም ሆነ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ስምሪት በተመለከተ  በተደጋጋሚ እየታየ ያለው አንዱ ችግር የፀጥታ አስከባሪዎች አንድ አካባቢን ለቅቀው መሄዳቸውን ተከትሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በመሆናቸው፤ የዚህን ችግር እጅግ አሳሳቢነት ኮሚሽኑ ከዚህ በፊትም ማሳወቁን አስታውሰው፣ “ግጭቱ ሙሉ በሙሉ ባሕሪውን በመቀየር ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳይለወጥ እና የአካባቢው ሰላምና ደህንነት ሙሉ በሙሉ እስከሚረጋገጥ ድረስ በቂ የፀጥታ ኃይሎች በተለይ ለግጭትና ጥቃት ተጋላጭ  የሆኑ አካባቢዎች ላይ በቋሚነት ተመድበው  መንግስት የሁሉንም ነዋሪዎች ደኅንነት የማስጠበቅና ከጥቃት መከላከል ግዴታና ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል፡፡  

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም፣  በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች  አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ አሳስበዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img