Tuesday, May 7, 2024
spot_img

በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ ኪራሙ ወረዳ ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ስምሪት እና እንቅስቃሴ የተመለከተ አሰራር ተገቢው ምርመራ ሊደረግበት እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 20፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ጊዳ ኪራሙ ወረዳ ነሃሴ 11 በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ፣ ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የ”ኦነግ ሸኔ” ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ማድረሳቸው በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ገልጧል፡፡

ኮሚሽን ነሃሴ 12 በታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት ከ150 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና መናገራቸውን አሳውቋል፡፡

በዚህም የተነሳ ሌላው የወረዳው ነዋሪዎች፣ በተለይም ሴቶችና ሕጻናት ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሸሻቸውንና በቀጣይ ቀናት ከነዋሪዎች የተውጣጡ ሰዎች ብሔርን መሰረት ያደረገ የአጸፋ ጥቃት በማድረሳቸው 60 ሰዎች መገደላቸውን፣ ነዋሪዎችም ወደ አማራ ክልልና ወደ ኪራሙ ከተማ መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ ተረድቻለሁ ነው ያለው፡፡

በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ወደ አከባቢው በመመለሳቸው ጊዳ ኪራሙ ወረዳ የተረጋጋ መሆኑን ነዋሪዎች ያስረዱ ቢሆንም በጊዳ ኪራሙና በሌሎች አጎራባች ወረዳዎች አሁንም ድረስ የፀጥታ ስጋት እንዳለም ነው ያመለከተው፡፡

ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ክትትሉን የሚቀጥል መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ የአካባቢው ፀጥታ የደረሰበት አስጊ ደረጃ ወደ አጎራባች አካባቢዎች እንዳይዛመትና የበለጠ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያደርስ አስቸኳይ እርምጃ አስፈላጊ መሆኑን አሳስቧል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በቀዳሚነት የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር እንዲቀናጁና የአካባቢውን ነዋሪዎች ደኅንነት እንዲያረጋግጡ እንዲሁም የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለጥቃቱ መፈፀም ክፍተት የፈጠረው የፀጥታ ሀይሎች ከአከባቢው መውጣት ምክንያቱን እንዲያጣሩ በአጽንዖት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አክለውም አሁንም ለታጣቂ ኃይሎች ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በዘላቂነት ወደነበረበት ለመመለስና የተቋረጡ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር እና የፀጥታ ኃይል በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ የፌዴራል መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ እና በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙ አካላትን የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የፌዴራልና የክልሉ ኃላፊዎች በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img