Sunday, November 24, 2024
spot_img

በአሰላ የሚገኘው የአህያ ቄራ በድጋሚ እንደተከፈተ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 1፣ 2014 ― በአሰላ ከተማ የዛሬ ሰባት ዓመት በ60 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ወደ ስራ ሊገባ ሲል ስራ ለማቆም የተገደደው በአሰላ የሚገኘው የቻይናዊያን የአህያ ቄራ መከፈቱ ተነግሯል፡፡

በቀን 300 አህዮችን የማረድ አቅም አለው የተባለው ቄራው፣ እስካሁን 80 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የአህያ ስጋ ወደ ውጭ የላከ ሲሆን፣ ቆዳዎቹን ወደ ቻይና ለመላክ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የፎርቹን ዘገባ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ከአሰላ ከተማ በተጨማሪ በቢሾፍቱ ከተማ ጭምር ለሁለት የቻይና ኩባንያዎች የአህያ ቄራ እንዲከፍቱ ፍቃድ ቢሰጥም የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድርጊቱ ከኢትዮጵያውያን ባህልና እሴት ጋር የሚጻረር ነው በማለት በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞ አቅርበው ነበር፡፡

ተቃውሞውን ተከትሎ ኮሚሽኑ ለሁለቱ ኩባንያዎች ከሰጠው ፍቃድ ውጭ ተጨማሪ አልሰጥም ሲል አሳውቆ ነበር፡፡ በወቅቱ ከተዘጉት መካከል የቢሾፍቱውን የአህያ ቄራ የሚያስተዳድረው የቻይናው ሻንዶንግ ዶንግ ኩባንያ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እያጤነ መሆኑን ለሚዲያዎች ቢናገርም የወሰደው እርምጃ ስለመኖሩ የተነገረ ነገር የለም፡፡

አሁን በአሰላ ሮንግ ቻንግ የሚል ስያሜ ያለው ድርጅት ወደ ስራ የገባው ወደ ኬንያ ለእርድ በኮንትሮባንድ የሚላኩ የአህዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ነው የተባለ ሲሆን፣ ስራ ከመጀመሩ በፊት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ማድረጉን ፎርቹን ዘግቧል፡፡

በአህያ እርድ የሚሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች በተመሳሳይ መልኩ በቡርኪናፋሶ፣ ናይጀሪያ እና ሌሎች ሃገራት ያቋቋሟቸው የአህያ ቄራዎች ተቃውሞ ቀርቦባቸው እንዲዘጉ መደረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከዚህ በተለየ ጎረቤት አገር ኬንያም ከፈረንጆቹ 2012 አንስቶ ከቻይና በኩል ባለው ከፍተኛ ፍላጎት ለአህያ ቄራ ፍቃድ ሰጥታ ስትሰራ የቆየች ቢሆንም፣ በአገሩ የሚገኙ የአህዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኗል በሚል ቄራዎቹ እንዲዘጉ ስትል ባለፈው ዓመት ወስናለች፡፡

የኬንያ ግብርና ሚኒስቴር ባለስልጣናት የአህዮቹ ቁጥር መቀነስ የለበትም ያሉት በገጠር አካባቢዎች ሴቶች ከወንዝ ውሃ ለመቅዳት እና በእንጨት ለቀማ ወቅት ስለሚጠቀሟቸው ቁጥሩ በዚያው ቀጥሎ ይበልጥ ከተመናመነ እነዚህ የገጠር ሴቶች ላይ ጫናው በቀጥታ ያርፋል በሚል ምክንያት ነበር፡፡ ይህንኑ የሚያስተጋባ የተቃውሞ ሰልፍ በአገሪቱ መዲና ናይሮቢ ተካሄዶም ነበር፡፡ በስምንት ዓመት ውስጥ የአህዮች ቁጥር ከ1 ነጥብ 8 ወደ 1 ነጥብ 2 የቀነሰባት የኬንያ የግብርና ሚኒስትር ፒተር ሙንያ፣ የአህያ እርድ የተፈቀደበትን ውሳኔ ቀድሞም ቢሆን ‹‹የተሳሳተ ነበር›› ብለውታል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img