Sunday, November 24, 2024
spot_img

የእነ ጃዋር መሐመድ ባቀረቡት አቤቱታ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ሳይሰሙ ቀሩ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 22፣ 2014 ― የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ተከሳሾች ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት የያዘው ቀጠሮ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ሳይሰማ የቀረበው የተከሳሽ ጠበቆች ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ መሆኑ ነው የተነገረው።

ከተከሳሽ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ከድር ቡሎ ነገሩኝ ብሎ ቢቢሲ እንደነገረው፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጃዋር መሐመድን ጨምሮ አራት ተከሳሾች በሌሉበት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ይሰሙ ሲል ያሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የቀረበው ይግባኝ መርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች እንዳይሰሙ ማዘዙንም ጠበቃው ከድር ቡሎ ተናግረዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ከዛሬ ሰኞ ጥቅምት 22፣ 2014 ጀምሮ ለመስማት ቀጠሮ ይዞ ነበር።

ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳና እና ደጀኔ ጣፋ “ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ በአስፈጻሚው አካል እየተከበረ አይደለም። ሥራ አስፈጻሚው አካል ሕግ እስካላከበረ ድረስ ፍርድ ቤት አንገኝም” በማለታቸው አራቱ ተከሳሾች በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበረ ይታወሳል።

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከሳሽ ጠበቆች አቤቱታን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለኅዳር 7፣ 2014 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ 24 ግለሰቦች አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

በዚህ የክስ መዝገብ ሥር የተካተቱት ተከሳሾች የፀረ ሸብር አዋጅ፣ የቴሌኮም አዋጅ፣ የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመተላለፍ ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img