Sunday, May 5, 2024
spot_img

እነ ጃዋር መሐመድ ለሁለት ዓመት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱን ጠየቁ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ግንቦት 12፣ 2013 ― የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የሚያካሂደውን ምርመራ አቋርጦ ምርጫው ካለፈ በኋላ ለ2015 እና 2016 ቀጠሮ እንዲሰጣቸው አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ጠየቁ። ሁለቱ ተከሳሾች ጥያቄውን ያቀረቡት ዛሬ ሐሙስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነበራቸው መደበኛ የክስ ሂደት የችሎት ውሎ ላይ ነው።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ዛሬ የተሰየመው በምስክሮች አሰማም ሂደት ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠውን የይግባኝ ውሳኔ ተመልክቶ ሂደቱን ለመቀጠል ነበር። ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ የጠቀሳቸው ምስክሮች በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙ ያቀረበው ጥያቄ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ነበር ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያለው።

ይግባኙን የተመለከተው ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት ወይስ ከመጋረጃ ጀርባ ይካሄድ የሚለውን የስር ፍርድ ቤት በድጋሚ እንዲመረምር በትላንትናው ዕለት ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ፤ የእነ ጃዋር መሐመድን መደበኛ ክስ ለሚመለከተው ችሎት በጊዜ እጥረት ምክንያት መድረስ አለመቻሉ በዛሬው የችሎት ውሎ ተገልጿል።

ችሎቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተመልክቶ ቀጣይ ሂደቱን ለመተግበር ለሚቀጠለው ሳምንት ረቡዕ ግንቦት 18 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ሆኖም ቀጠሮው በአካል በችሎት በተገኙ ተከሳሾች ዘንድ ተቃውሞ ቀርቦበታል።

በመጀመሪያ ተቃውሟቸውን ያሰሙት አቶ በቀለ ገርባ ቀጠሮ ምንም ፋይዳ ስለሌለው ፍርድ ቤቱ ግንቦት 18 ቀጠሮ ከሚሰጥ ይልቅ ከሁለት ዓመት በኋላ ለ2015 ወይም 2016 ቢሰጥ ይሻላል ብለዋል። ‹‹ሰው በአደባባይ በሚረሸንበት አገር ፍርድ ቤት መቅረብ እድለኝነት ነው›› ያሉት አቶ በቀለ ገርባ፤ ይህም ሆኖ ግን ምንም ፍትህ ለማይገኝለት ነገር ፍርድ ቤት መመላለስ እንደሌለባቸው ጠቅሰዋል።

አንድ ዓመት ሙሉ ያለምንም ፍትህ ፍርድ ቤት እየተመላለሱ እንደነበር የተናገሩት አቶ በቀለ፤ ‹‹ፍርድ ቤት በነፃ ቢያሰናብትም እንኳን በፖሊስ ተይዞ ደብዛው የሚጠፋበት ሀገር ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል። ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ምርጫውን አሳልፎ እስከ ሁለት አመት ድረስ ረዘም ያለ ቀጠሮ ቢሰጥ ደስ እንደሚላቸው ተናግረዋል። አቶ በቀለ ይሄንን አቤቱታቸውን ሲጨርሱ ሌሎች ተከሳሾች በጭብጨባ አጅበዋቸዋል።

ይህንኑ ተቃውሞ ደግፈው የተናገሩት አቶ ጃዋር መሐመድ ‹‹እናንተ ነፃ ናችሁ ብትሉንም እነሱ ግን አይለቁንም›› በማለት ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። በተጨማሪም መንግስት የሚፈልገው የእኛን መታሰር ስለሆነ የፍርድ ቤቱንም የእኛንም ጊዜ ከምንገድል ከሁለት አመት በኋላ ቀጠሮ ቢሰጥልን ይሻላል ሲሉ ተደምጠዋል።

‹‹ወይ ከስልጣን ወርደው ወይ ደግሞ አሁን ያለው የፖለቲካ ፎርሙላ ተቀይሮ እንስክናይ ድረስ፤ ፍርድ ቤት መመላለስ ትርጉም የለውም›› ብለዋል። ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ነጻ ተብለው ተመልሰው የተያዙ ሰዎች መኖራቸውንም ሀሳባቸውን ለማጠናከሪያነት ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የፍርድ ቤት ስልጣን መነጠቅ እንዳለ የተናገሩት አቶ ደጀኔ ጣፋ ‹‹ፖሊስ እኛ እና ፍርድ ቤት አንድ ነን ብሏል›› ሲሉ ተናግረዋል። አሁን ባለው ሁኔታም ፍርድ ቤት እራሱን ማስከበር አልቻለም ያሉት አቶ ደጀኔ ‹‹የዚህ ፍርድ ቤት መከበር የኛም መከበር ነው›› ብለዋል።

አቶ ደጀኔ ‹‹ደካማ ፍርድ ቤት ስላለን ይህቺ ሀገር ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ እየገባች ነው” በማለት እንደ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። በመጨረሻም ‹‹ለዚህች ሀገር ዲሞክራሲ ስንል እድሜ ልካችንን ተንከራተናል›› ያሉት አቶ ደጀኔ ማንንም እንዳልበደሉ እና እንዳልዘረፉ ለፍርድ ቤት አስረድተዋል። በተከሳሾች አቤቱታ ላይ አስተያየት የሰጠው ዐቃቤ ህግ በፍርድ ቤቱ የተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ አግባብ ነው ብሏል። ‹‹ችሎቱ ሌሎች ፍላጎቶቻችንን ማንጸባረቂያ መሆን የለበትም›› በማለትም አሳስቧል።

የተከሳሾችን አቤቱታ ያደመጠው ፍርድ ቤትም የሚሰጡትን ትዕዛዞች ለማስከበር እስከመጨረሻው እየሰራ እንደሆነ ገልጿል። በሌሎች ተከሳሾች ላይ የተፈጠረው ችግር በተመሳሳይ መልኩ ይፈጠራል ብሎ እንደማያምንም አስረድቷል። በመሆኑም ቀጣይ ሂደቶችን ለመወሰን ለግንቦት 18 የተሰጠው ቀጠሮ እንደተጠበቀ ይቆያል ብሏል።

በዛሬው ችሎት ጉቱ ባይሳ እና ሸምሰዲን ጣሃ እና የተባሉት ተከሳሾች የህክምና አገልግሎት ማግኘት እና ከቤተሰቦች ጋር በስልክ መገናኘትን በተመለከተ ተጨማሪ አቤቱታ አቅርበዋል። አቤቱታዎቹን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ማረሚያ ቤት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቷል ሲል የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ ገጽ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img