Saturday, May 18, 2024
spot_img

የእነ ስብሐት ነጋ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደት በሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀርብ እንደሆነ ለመርመር ቀጠሮ ተሰጠ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 13፣ 2013 ― የእነ አቶ ስብሐት ነጋ ጠበቆች በቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደት ላይ ያቀረቡት አቤቱታ፤ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀርብ ወይም አያስቀርብ እንደሆነ ለመወሰን ለሰኞ ግንቦት 16 ቀጠሮ ተሰጥቷል። ቀጠሮውን የሰጠው ዛሬ የተሰየመው አንደኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ነው።

የተጠርጣሪ ጠበቆች አቤቱታውን ለሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት፣ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደትን በተመለከተ የፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰኗቸውን ውሳኔዎች በመቃወም ነው።

አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ 42 ተጠርጣሪዎችን የወከሉት ጠበቆች አቤቱታቸውን በጽሑፍ ለሰበር ሰሚ ችሎት ያስገቡት ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ግንቦት 11 ነበር።

ከጠበቆቹ መካከል ሦስቱ ጉዳዩን ለማድመጥ ዛሬ ለተሰየመው ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን በዝርዝር አስረድተዋል። ጠበቆቹ በማብራሪያቸው በስር ፍርድ ቤቶች የተላለፉት ውሳኔዎች “መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለባቸው” በማለት ውሳኔዎቹ ስምንት የህግ ስህተቶች እንዳሉባቸው በመጠቆም ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል።

በአቤቱታው ከተነሱ መሰረታዊ የህግ ስህተቶች መካከል፤ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔዎች “ለምስክሮች ጥበቃ ሲደረግ ሊሟሉ የሚገባቸውን መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች እና ስነ ስርዓታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ የተሰጠ ነው” የሚለው በዋነኛነት ተጠቅሷል። ጠበቆቹ ይህን ሲያስረዱ “ፍርድ ቤቱ የተረጋገጠ ነገር ሳይኖር ግምት በመውሰድ ብቻ የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት አለበት” ብለዋል።

ለምስክሮች ጥበቃ ማድረግ የሚቻለው ምስክሩ የሚያስረዳው ነገር በሌላ በማንኛውም ሁኔታ መረጋገጥ የማይችል ከሆነ እንደው ያስታወሱት ጠበቆቹ፤ የስር ፍርድ ቤት ግን “ይህን ሳያመዛዝን ግምት በመውሰድ ብቻ ውሳኔ አስተላልፏል” ብለዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በተመለከተበት ወቅት ዐቃቤ ህግ ለምስክሮች ደህንነት ሲል ጥበቃ በማድረጉ ምክንያት የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደቱ በዝግ ችሎት እንዲሆን መጠየቁን ጠበቆቹ በአቤቱታቸው አንስተዋል።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ወደ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መልሶ ክርክር እንዲደረግበት ከታዘዘ በኋላ ግን ዐቃቤ ህግ ቀደም ሲል በክርክሩ ላይ የጠቀሰውን ምክንያት “ለሀገር ደህንነት ሲባል ነው” በሚል መቀየሩን ጠቅሰዋል። የታችኛው ፍርድ ቤትም ይሄንኑ መነሻ በመድረግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እንዲሆን መወሰኑ ተገቢ አይደለም ሲሉም አክለዋል።

በተጨማሪም ዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እንዲሆን የፈለገው “ሚዲያዎች አዛብተው እንዳይዘግቡ” በሚል እንደሆነ ጠበቆች አስታውሰዋል። ነገር ግን ሚዲያ እንዳይዘግብ ማድረግ እና ዝግ ችሎት ይሁን ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው ያሉት ጠበቆቹ፣ ሚዲያ እንዳይዘግብ ከተፈለገ ዝግ ችሎት ሳይሆን በሌላ መንገድ መከልከል ይቻላል ብለዋል።

ሚዲያዎችን እንዳይዘግቡ ሲባል ብቻ ችሎቱ በዝግ መሆን የለበትም ሲሉ የተከራከሩት ጠበቆች “መረጃ ከኛ ጠይቀው ሊዘግቡ ይችላሉ ” ብለዋል።

የጠበቆቹን ማብራሪያ ያደመጠው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንደኛ ሰበር ሰሚ ችሎት፣ ጉዳዩ ለምርመራ ያስቀርብ ወይም አያስቀርብ እንደሆነ ለመወሰን ለሰኞ ግንቦት 16 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ችሎቱ በዚሁ ዕለት በተጠርጣሪ ጠበቆች የቀረበ የእግድ ጥያቄን እንደሚመለከትም አስታውቋል።

የእግድ አቤቱታው፤ የፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን በዝግ ችሎት ለመስማት የያዘው ቀጠሮ በተያዘለት ቀን እንዳይካሄድ የሚጠይቅ መሆኑንም የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ ገጽ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img