አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 30፣ 2013 ― በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከአራት ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል፡፡
ዶይቸ ቬለ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል ብሎ እንደዘገበው የታጠቁ ቡድኖች ዓርብ እለት ስድስት የፀጥታ አባላትን ገድለው ወደ መንደሮቹ ከገቡ በኋላ ከ4 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።
ታጣቂዎች ባለፉት ሁለት ቀናት ማለትም ቅዳሜና እሑድ በወረዳው ጋቢጣና ሰመርታ በተባሉ ቀበሌዎች የቆርቆሮና የሳር መኖሪያ ቤቶችን አቃጥለዋል፣ በማሳ ላይ የነበረ ሰብልም አውድመዋል ነው የተባለው፡፡
በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን የጉራፈርዳ ወረዳ የፀጥታ ባለስልጣናት በበኩላቸው ቁጥር ባይጠቅሱም በወረዳው በፀጥታ አባላት ላይ ጥቃት መድረሱንና የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን አረጋግጠዋል።
የጉራፈርዳ ወረዳ የሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቅነህ እሸቱ «ዓርብ እለት ወሃ ለመቅዳት በጉዞ ላይ በነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ በደፈጣ በተደረገ ጥቃት የሞትና የመቁሰል ጉዳት ደርሷል። ታጣቂዎቹ ወደ መንደሮች ዘልቀው በመግባት የመኖሪያ ቤቶችንም አቃጥለዋል» ብለዋል።
የሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ወረዳው ከደቡብ ሱዳንና ከጋምቤላ ክልል ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ታጣቂዎቹም ወደ እነኚሁ አካባቢዎች በመሸሽ ተመልስው ጥቃት እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል፡፡
አብዛኞቹ ታጣቂዎችም ቀደም ሲል እርሳቸው ጁንታው ሲሉ የጠሩት ቡድን አካባቢውን ለመረበሽ ያስታጠቃቸው ናቸው። ‹‹መንግስት ወረዳው እንዲረጋጋ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ነው። የፀጥታ ኃይሉም መስዋዕትነት እየከፈለ›› ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ታጣቂዎች በነዋሪዎችና በፀጥታ አባላት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲያደርሱ መቆየታቸው ይታወቃል።
የጉራፈርዳ ወረዳ በመጪው ሰኔ 14 ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ ድምፅ ከማይሰጥባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሳምንት በፊት ይፋ ማድረጉን ዘገባው አስታውሷል፡፡