Saturday, November 23, 2024
spot_img

በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የምስክሮች አሰማም ሂደት በድጋሚ እንዲመረመር ፍርድ ቤት ወሰነ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 11፣ 2013 ― የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ጀዋር መሐመድ መዝገብ የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት ወይስ ከመጋረጃ ጀርባ ይካሄድ የሚለውን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በድጋሚ እንዲመረምር ዛሬ ውሳኔ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ፤ ዐቃቤ ህግ በምስክሮች ላይ ሊደርስባቸው ይችላል ያላቸውን በቂ እና አሳማኝ አደጋዎች በዝርዝር ለከፍተኛው ፍርድ ቤት እንዲያቀርብም አዝዟል።

ዐቃቤ ህግ ከዚህ ቀደም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነበረ ችሎት፤ ለምስክሮች ጥበቃ ማድረጉን ገልጾ የምስክሮች አሰማም ሂደቱ በዝግ ችሎት፣ ከመጋረጃ ጀርባ እና የምስክሮች ማንነት ሳይገለጽ እንዲሆን ጠይቆ ነበር። ዐቃቤ ህግ በምስክሮች ላይ ይደርሳል ብሎ ያሰበውን አደጋ በዝርዝር አላስረዳም ያለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት፤ የዐቃቤ ህግ ጥያቄን ውድቅ በማድረግ የምስክሮች አሰማም ሂደቱ በግልጽ ችሎት እንዲሆን ብይን ሰጥቷል።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔን የተቃወመው ዐቃቤ ህግ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመውሰድ ይግባኝ ጠይቋል። ይግባኝ የቀረበለት ጠቅላይ ፍርድ ቤትም በዐቃቤ ህግ እና በተከሳሽ ጠበቆች በኩል የተነሱ ሀሳቦችን ከመረመረ በኋላ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 11 በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።

ዐቃቤ ህግ ለምስክሮች ጥበቃ በማድረጉ ብቻ ማስረጃ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ሳይጠበቅበት በዝግ ችሎት እና በመጋረጃ ጀርባ እንዲሆን የጠየቀበትን አግባብ የተመለከተው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል። ፍርድ ቤት፤ ህገ መንግስቱን፣ የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅን እንዲሁም የአለም አቀፍ ህጎችን መርምሮ ውሳኔ የመስጠት ሚና እንዳለውም በውሳኔው ላይ አመልክቷል።

ዐቃቤ ህግ በቂ ማስረጃዎችን ባለማቅረቡ፤ የምስክር አሰማም የችሎት ሂደቱ በግልጽ እንዲካሄድ በስር ፍርድ ቤት የተላለፈው ውሳኔ ተገቢነት በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ቢያገኝም፤ ውሳኔው ላይ ግን ማሻሻያ መደረግ አለበት ተብሏል። በዚህም መሰረት፤ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በዐቃቤ ህግ በኩል የሚቀርቡለትን፤ በምስክሮቹ ላይ ሊደርስ ይችላሉ የተባሉ አደጋዎችን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ተቀብሎ፤ አግባብነታቸውን ከመረመረ በኋላ ተገቢውን ብይን እንዲሰጥ ተወስኗል።

በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከፈተው ክስ በዚህ ይግባኝ ምክንያት መደበኛ ሂደቱ ተስተጓጎሎ ቆይቷል። ፍርድ ቤቱ መደበኛውን የክስ ሂደት ለመመልከት ለነገ ሐሙስ ግንቦት 12 ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።

በዛሬው የጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ችሎት ተከሳሾች በአካል አልቀረቡም። ከዚህ ቀደም በሌሎች የይግባኝ ችሎቶች እንደታየውም ባሉበት ሆነው በፕላዝማ የቪዲዩ ግንኙነት አማካኝነትም ችሎቱን አልተከታተሉም ሲል የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img