Sunday, October 6, 2024
spot_img

በምዕራብ ኦሮሚያ የዞን አመራርን ጭምሮ 5 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 9፣ 2013 ― የቀድሞ የምዕራብ ወለጋ ዞን ጸጥታ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ አምስት የመንግሥት ሠራተኞች በታጣቂዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ።

እነዚህ አምስት ሰዎች የተገደሉት ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ከቆንዳላ ወረዳ ወደ መንዲ እየተጓዙ እንደነበረ የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደሪ አቶ ኤልያስ ኡመታ ነግረውኛል ብሎ ቢቢሲ አስነብቧል።

ለሥራ ጉዳይ በመጓዝ ላይ የነበሩትን የቀድሞው የጸጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ ዋቅጋሪ ቀጄላና ሌሎች ባልደረቦቻቸውን የገደሉት ታጣቂዎች፤ “እራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብለው የሚጠሩት በቅርቡ ደግሞ መንግሥት አሸባሪ ሲል የፈረጃቸው የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው” ሲሉ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል።

የአምስቱ ሰዎች የመገደል ዜና የተሰማው ከአንድ ሳምንት በፊት አባ ቶርቤ በተባለ ቡድን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ መገደልን ተከትሎ የቡድኑ አባል ነው የተባለ ወጣት በመንግሥት የጸጥታ ኃይል በአደባባይ ከተገደለ በኋላ ነው።

አቶ ኤልያስ እንዳሉት ቅዳሜ ዕለት በታጣቂዎች የተገደሉት አምስቱ ሰዎች በሁለት መኪና ሆነ እየተጓዙ ሳሉ ጥቃቱ እንደተፈጸመባቸው አስረድተዋል።

ከዞን አመራር በተጨማሪ አንድ አሽከርካሪ እና ጥበቃ ለማድረግ ከዞን አመራሩ ጋር አብረው ሲጓዙ የነበሩ ሁለት የሚሊሻ አባላት እና አንድ የኦሮሚያ ፖሊስ አባል መገደላቸውን ተነግሯል።

ከሟቾቹ መካከል የቀድሞው የዞን አመራር የቀብር ሥርዓት ትናንት መፈጸሙን የተገለጸ ሲሆን፣ እስካሁን ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው አለመኖሩን የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

አምስቱ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት የተፈጸመው ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚዋሰኑበት ስፍራ መሆኑን አቶ ኤልያስ አመልክተው፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ በአካባቢው የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ፍተሻ እያደረጉ ነው ብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img