Sunday, November 24, 2024
spot_img

በማኅበር ቤት ለመገንባት የተመዘገቡ ነዋሪዎች የሚደራጁት ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በኋላ ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 4፣ 2013 ― የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ቢሮ በአማራጭነት ያቀረባቸው የ20/80 እና የ40/60 የቤት ተመዝጋቢዎች በማኅበር ተደራጅተው ቤት እንዲገነቡ የሚያስችለው መርሐ ግብር አንድ አካል የሆነው ተመዝጋቢዎችን የማደራጀት ሥራ፣ ከ14ኛው ዙር የጋራ ቤቶች ዕጣ ማውጣት በኋላ እንደሚከናወን ተነግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማራጭ የቤት ልማት አቅርቦት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ ታምራት ነግረውኛል ብሎ ሪፖርተር እንደዘገበው፣ ተመዝግበው የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ያልወጣላቸው ነዋሪዎችን በማኅበር ለማደራጀት ሲካሄድ የቆየው ምዝገባ ከሁለት ሳምንት በፊት ተጠናቋል፡፡ ለአማራጩ የተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎችም 12 ሺሕ 609 እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ለባለዕድለኞች ማስተላለፍ በቅርቡ እንደሚከናወን ያስታወቁት አቶ ጳውሎስ፣ ሆኖም ትክክለኛውን ቀን መቼ እንደሆነ ለመናገር እንደሚያዳግታቸው ተናግረዋል፡፡

የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓቱ ከተከናወነ በኋላ ተመዝጋቢዎችን ለማደራጀት ያስፈለገበት ምክንያት የዕጣው ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ዕድል ለማመቻቸት ታስቦ እንደሆነ ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ እስከዚያው ድረስ ግን ለግንባታ አገልግሎት የሚውሉ ቦታዎችንና ከባንክ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማስተካከል እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ተመዝጋቢዎች በጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣው ዕድለኛ ከሆኑ ከምዝገባው ዝርዝር በቀጥታ እንደሚወጡና የከተማው ቤቶች አስተዳደር ቢሮ የቀሩትን ተመዝጋቢዎች በቀጥታ የማደራጀቱን ሥራ እንደሚያከናውን፣ የመሬት ድልደላውም በዚያው መሠረት በተመረጡት አምስት ክፍላተ ከተሞች የሚከናወን እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ በመጋቢት 2013 የቁጠባ ክፍያቸውን ያላቋረጡ የ2005 የ40/60 እና የ20/80 ተመዝጋቢዎች በማኅበር ተደራጅተው፣ የጋራ መኖሪያ ቤት ለመሥራት እንዲችሉ የሚያደርግ መመርያ አዘጋጅቶ የበይነ መረብ ምዝገባ ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img