Friday, May 3, 2024
spot_img

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ማስጀምር አልቻለም ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ነሐሴ 25፣ 2013 ― የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በገንዘብ እጥረት ምክንያት በአዲሱ የበጀት ዓመት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ማስጀምር እንዳልቻለ ተሰምቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በቀጣይ አምስት ዓመታት 1 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት እቅድ እንዳለው አሳውቆ የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት የከተማው ቤቶች ልማት ቢሮው የመጀመሪያዎቹን 99 ሺሕ የ20/80 እና 40/60 ቤቶች ግንባታ ለማስጀመር አቅዶ ቢንቀሳቀስም በገንዘብ እጥረት ሰበብ ውጥኑ በእንጥልጥል ላይ እንደሚገኝ ካፒታል ጋዜጣ ይዞት የወጣው ዘገባ ያመለክታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ለቤቶቹ ግንባታ የጠየቀውን 89 ቢሊዮን ብር እና 512 ሔክታር መሬት እስካሁን ድረስ እንዲለቀቅለት እየጠበቀ ቢሆንም፣ ሊቀርብለት አልቻለም ነው የተባለው፡፡

ቢሮው የጠየቀው አቅርቦት ስላልተሟላለት የቤቶቹን ግንባታ ባይጀምርም፣ በእጁ የሚገኙትን ቀድሞ የተጀመሩ ቤቶችን ግንባታ ለመጨረስ እንደሚሠራ ነው የተነገረው፡፡ በአዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት ያላለቁ 139 ሺሕ 8 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 51 ሺ 229 ቤቶች ከሁለት ዓመት በፊት እጣ ለደረሳቸው የተላለፉ ናቸው፡፡ ሌሎች 22 ሺሕ ቤቶች ደግሞ በልዩ ሁኔታ ሲተላለፉ፣ ቀሪዎቹ በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡

የከተማው አስተዳደሩ ቤቶች ልማት ቢሮ በተጠናቀቀው የ2013 የበጀት ዓመት የጀመራቸው ቤቶች 4 ሺሕ 287 ብቻ መሆናቸው ሲነገር፣ ይሕም ከታቀደው አፈጻጸም 7 ነጥብ 9 ብቻ ነው፡፡ ቤቶቹን የሚገነባው ተቋራጭ ለዚህ ዝቅተኛ አፈጻጸም የግንባታ አቅርቦት ማነስን እንደ ምክንያት ማቅረቡ ተጠቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከወራት በፊት አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የከተማው ነዋሪዎችን የቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት በሚል ከአንድ የደቡብ አፍሪካ የቤት አልሚ እንዲሁም ዋዲ አል ሲደር ከሚባል ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈጸማቸው መነገሩ ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img