Saturday, May 18, 2024
spot_img

መጀሊስ ከአንድ ዓመት በኋላ አካሄደዋለሁ ላለው ምርጫ ከመንግሥት እገዛ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፤ ሐሙስ መጋቢት 12 2016 – የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ከአንድ ዓመት በኋላ አካሄደዋለሁ ላለው ምርጫ መንግሥት እገዛ እንዲያደርግለት የጠየቀው በፕሬዝዳንቱ በኩል ነው፡፡

ፕሬዝዳንቱ ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ማክሰኞ መጋቢት 10፣ 2016 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮችና ከሁሉም ክልሎች የመጡ አባቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ፕሬዝዳንት ሆነው ለሦሰት ዓመታት ሲመሩ የቆዩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ እና ምክትላቸውን ዶ/ር ጄይላን ኸድር እንዲሁም ጸሐፊውን በማንሳት በምትካቸውም ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋን በፕሬዝዳንት፣ ሸይኽ ዓብዱልከሪም በምክትልነት እንዲሁም ሸይኽ ኑረዲን ደሊል ጸሐፊ አድርጎ የሾመው በሐምሌ 2014 ነበር፡፡  

ይህ ጉባዔ ለአዲሶቹ ተሹዋሚዎች የሰጠው ጊዜ 3 ዓመት የነበረ ሲሆን፣ ይኸው አመራር በሐምሌ ወር አጋማሽ 2 ዓመት ይደፍናል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው ውይይት ላይ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፤ ጊዜው ሲደርስ ‹‹ከሕዝብ ነው የተረከብነው፤ ለሕዝብ እናስረክባለን›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ከመጅሊስ ላይ ‹‹መቶ በመቶ እጁን አንስቶ›› በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በቀጣይ ምርጫ መንግሥት እንዲያግዛቸው ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ፕሬዝዳንቱ ይህን ጥያቄ ባቀረቡበት ጊዜ ‹‹ጣልቃ ገብ እንድትሆኑ›› አይደለም ብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ እንደ መንግሥት መጪው ምርጫ ላይ አግዙን የምንለው ‹‹አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ እንድታመቻቹልን ነው›› ሲሉ ከመንግሥት የሚፈልጉትን እገዛ አብራርተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img