- ፖሊስ ለተቃውሞ የወጡ ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል
አምባ ዲጂታል፤ ሰኞ መጋቢት 11፣ 2015 – በምሥራቅ አፍሪካዋ አገር ኬንያ ኑሮ ተወደደብን ያሉ ዜጎች ዛሬ ሰኞ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ተነግሯል፡፡
በአገሪቱ በኑሮ መወደድ እና በሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶች ዛሬ የተካሄደው ተቃውሞ ባለፈው ዓመት በምርጫ በተሸነፉት ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዶንጋ የተጠራ ነበር፡፡ በቂሊያም ሩቶ የተሸነፉት ኦዶንጋ ባለፉት ቀናት አንስቶ ለተቃውሞ ሲቀሰቅሱ የቆዩ ሲሆን፣ ፖሊስ ግን ትላንት እሑድ ፍቃድ የተሰጠው ተቃውሞ የለም በሚል እርምጃ እንደሚወስድ አስጠበንቅቆ ነበር ተብሏል፡፡
ሬውተርስ እንደዘገበው ዛሬ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በተለይ ኪቢራ በተባለ አካባቢ የኦዲንጋን ጥሪ የተቀበሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ድንጋይ ሲወረውሩ ነው የነበሩ ሲሆን፣ ፖሊስ በአጸፋው አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል፡፡
በዛሬው ተቃውሞ ቢያንስ አራት የፓርላማ አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ ሲነገር፤ በተቃውሞ አድራጊ ዜጎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም፡፡
ተቃውሞ ያስተናገዱት ከስድስት ወራት በፊት ሥልጣን የተረከቡት የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከተቃውሞው አስቀድሞ በአሁኑ ወቅት የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ የሚያበቃ ምንም ምክንያት እንደሌለ ተናግረው ነበር፡፡ በአንጻሩ ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋን በአገሪቱ ግጭት እና ብጥብጥ ለመፍጠር ይፈልጋሉ ሲሉ ከሰዋቸዋል፡፡
ዊሊያም ሩቶ ከወራት በፊት ሥልጣን ላይ ሲወጡ የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል ቃል የገቡ ቢሆንም፤ ባለፈው የፈረንጆቹ ፌብርዋሪ ወር ላይ በአገሪቱ የዋጋ ግሽበት 9.2 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡