Thursday, May 2, 2024
spot_img

በምዕራብ ትግራይ የጦር ወንጀል ማስረጃዎች እንዲጠፉ እየተደረገ መሆኑ ተዘገበ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 29 2014 ― በምዕራብ ትግራይ ውስጥ የተፈጸመ የዘር ማጽዳትን ለመሸፈን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አስከሬን በፀጥታ አካላት እንደተቃጠለ ነው ሲል የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

15 የዓይን እማኞች ቃለ ምልልስ ተደርገዋል በተባለበት የዜና ተቋሙ ዘገባ፣ ‹‹የዘር ማጽዳት መከናወኑን ለመሸፈን በተደራጀ ሁኔታ፣ ማስረጃዎችን ለማጥፋት ሲባል›› የሰዎች አስከሬን እየተቃጠለ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡

ይህ አስከሬን የማቃጠል ክስ የመጣው የቀድሞው የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ፋቱ ቤንሱዳ የሚመሩት የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ የመርማሪዎች ቡድን እንደሚሰማራ በሚጠበቅበት ወቅት ነው፡፡

የምዕራብ ትግራይ አጎራባች የሆነው የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር ባደረጓቸው የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሎቹ አዳዲስ የጅምላ ግድያ መቃብሮችን እየቆፈሩ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡

የዓይን እማኖቹ እነዚህ የፀጥታ አካላት መቃብሮቹን ቆፍረው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስከሬን እንዳወጡና አስክሬኖቹን አቃጥለው አመዱን ከአካባቢው እያስወጡ ገልጸዋል መባሉንም ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል፡፡

የዜና ተቋሙ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቢጠየቅም፤ ምላሽ አላገኘሁም ያለ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሩና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤው አገኘሁ ተሻገር፣ ማስረጃ በስልት እየተወገደ ነው የሚለውን ክስ አጣጥለውታል ብሏል፡፡

አቶ አገኘሁ የመቃብር ቁፋሮ እየተደረገ እንደሆነ በማመን፣ በመቃብር ቁፋሮው የተገኙት አስከሬኖች ባለፉት 40 ዓመታት የተገደሉ የአማራ ተወላጆች እንደሆኑ ተናግረዋል።

አቶ አገኘሁ ‹‹ህወሓት አገሪቱን እየመራ ስለነበር እነዚህን የጅምላ መቃብሮች ቆፍሮ አስከሬኖቹን ለዓለም ማሳየት አልተቻለም ነበር›› ብለዋል። አያይዘውም በምዕራብ ትግራይ የዘር ማጽዳት ተካሂዷል የሚለውን ውንጀላ እንዲሁም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የሂውማን ራይትስ ዋችን ሪፖርት አጣጥለዋል፡፡ ሪፖርቶቹንም ‹‹ሐሰት ናቸው። መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘቡ ሪፖርቶች ናቸው›› ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገር ግን ቢቢሲ በዘገባው የጠቀሳቸው በሁመራ የሚኖሩ የወልቃይት ተወላጅ፤ ‹‹በሁመራ ከተማ ከሚገኘው ሐምሌ ሐሙሽተ ትምህርት ቤት ጀርባ ባለው አካባቢ 200 የትግራይ ተወላጆች በጅምላ ተቀብረዋል። እነዚህ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ወራት የተገደሉ ንጹሃን ናቸው›› ሲሉ ተናግረዋል።

የዓይን እማኞች የአማራ ሚሊሻዎች እና ፋኖ አስክሬኖቹን ቆፍረው አወጡ የሚሉት መጋቢት 26፣ 2014 ነው፡፡ በዘገባው የተጠቀሱ የዓይን እማኝ ‹‹እንጨት ሰብስበው ከዚህ ቀደም ዓይተን የማናውቀው ነገር አፈሰሱና የሰበሰቡትን አስክሬኖቹን አቃጠሉ። ከዚያ አስክሬኖቹ አመድ ሆኑ›› ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡

በአንጻሩ ከዚህ ቀደም የጎንደር ዩኒቨርስቲ አጥኚዎች የጅምላ መቃብሮች እንዳገኙና 12ቱ የጅምላ መቃብሮች ላይ ምርምር እያደረጉ እንደሆነ ተገልጾ ነበር። ሆኖም የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች በአጠቃላይ የጅምላ ግድያ በመፈጸም ይወነጀላሉ።

ባለፈው ኅዳር የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፣ ሁሉንም የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች የሚመረምር ገለልተኛ ቡድን ለማቋቋም ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን በማጣጣል ትብብር እንደማያደርግ ገልጿል። የተመድ ውሳኔ ‹‹ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር ያለመ ነው›› ሲልም መንግሥት ተቃውሞውን አስታውቆ ነበር።

ለምርመራ ቡድኑ የሚውል ገንዘብ እንዳይሰባሰብ ለማድረግ መጋቢት ላይ ኢትዮጵያ ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። ሩሲያ እና ቻይና የፌደራል መንግሥትን መደገፋቸውም ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img