Friday, May 17, 2024
spot_img

በምዕራብ ትግራይ የሰላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት በመንግሥት እና ሕወሓት ስምምነት ውስጥ እንዲካተት ሁለት የመብት ተሟጋቾች ጠየቁ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ መጋቢት 28 2014 በምዕራብ ትግራይ በአፍሪካ ኅብረት የተመራ የሰላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት በመንግሥት እና ሕወሓት ስምምነት እንዲካተት የጠየቁት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች የሆኑት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ናቸው፡፡

ሁለቱ የመብት ተሟጋቾች ይህንኑ በዛሬው እለት መጋቢት 28፣ 2014 ባወጡትና ላለፉት 15 ወራት ያካሄዱትን ምርመራ ውጤት በያዘው ‹‹ከዚህ ምድር እናስወግዳችኋለን፡ በሰብዓዊነት የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት በኢትዮጵያዋ ምዕራብ ትግራይ ዞን›› በተሰኘው ባለ 240 ገጽ ሪፖርት ላይ አስፍረዋል፡፡

ተቋማቱ በሪፖርታቸው በሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ምዕራብ ትግራይ በአስቸኳይ ማሰማራትን ያጠቃለለ እንዲሆን ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

እንደ መብት ተሟጋቾቹ ከሆነ የሰላም አስከባሪ ኃይል በስፍራው መሰማራት፤ የሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ፣ የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ እና በትግራይ አደጋ ላይ የወደቁ ሰዎችን ለመድረስ ቁልፍ ርምጃ ይሆናል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ወች የሰላም አስከባሪ ኃይሉ እንዲገባ የጠየቁት በአካባቢው ያለው ችግር ውስብስብ እና በቀላሉ የማይፈታ ስለሆነ ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ በሁለቱም ወገን ያሉ ሲቪሎችን ሊከላከል ይችላል የሚል ምክንያት በማቅረብ ነው፡፡

ሁለቱ የመብት ተቋማት ባወጡት ሪፖርት ላይ ከትግራይ ጦርነት መጀመሪ አንስቶ የተለያዩ ጉዳዮችን የዳሰሱ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል በጦርነቱ የመጀመሪያ ጥቂት ወራት ውስጥ የትግራይ ሚሊሻዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪ ሲቪሎች በማይካድራ ከተማ አካባቢው ነዋሪ በሆኑ እና ለቀን ስራ በመጡ የአማራ ተወላጆች ላይ የጦር ወንጀሎችን መፈጸማቸውን አስታውሷል።

ተቋማቱ በዝርዝር ካጠኗቸው ልዩ ክስተቶች መካከልም በተከዜ ድልድይ አካባቢ በጥር ወር 2013 ፋኖ በመባል በሚጠራው ሚሊሻ ተፈጽሟል ሲሉ የገለጹት ጭፍጨፋ ይገኝበታል።

ጥር 9 አዲ ጎሹ ተብላ በምትጠራው አነስተኛ ከተማ የፋኖ ሚሊሻዎች ነዋሪዎችን ከሰበሰቡ በኋላ ወንዶቹን በመምረጥ አስረዋል ያለው ሪፖርቱ፣ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በበኩላቸው 60 የሚጠጉ የትግራይ ተወላጅ ወንዶችን የተከዜ ድልድይ ጋር ወስደው ረሽነዋል ይላል።

ሪፖርቱን በተመለከተ የተናገሩት የአምነስቲ ዋና ጸሐፊ አግነስ ካላማርድ ‹‹የኢትዮጵያ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች በምዕራብ ትግራይ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎችን ክብደት ለማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል›› ሲሉ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡

አክለውም ‹‹የሚመለከታቸው መንግሥታት እየተካሄደ ያለው የዘር ማጽዳት ዘመቻን ማስቆም ብሎም ከአካባቢው የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችን በፈቃዳቸው እና ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ማስቻል አለባቸው›› ሲሉ ዋና ጸሐፊዋ ጥሪ አቅርበዋል።

ሪፖርቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እና የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ያሉት ነገር ባይኖርም፣ የሕወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ አስተያየት ሳይሰጡ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ አጋርተውታል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img