Sunday, May 19, 2024
spot_img

ከመቐለው አይደር ሆስፒታል በቀን እስከ 6 አስከሬኖች እንደሚሸኙ ተዘገበ

አምባ ዲጂታል፤ ቅዳሜ ሚያዝያ 15 2014 በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ የሚገኘው ዋነኛ የሕክምና ተቋም አይደር ሪፈራል ሆስፒታል በቀን ከ4 እስከ 6 አስክሬኖች የሚሸኝበት ደረጃ እንደደረሰ ተነግሯል፡፡

በመድኃኒትና ሕክምና አገልግሎት እጥረት ከሞቱት መካከል የሆስፒታሉ የጤና ባለሞያዎች እንደሚገኙበትም አስታውቋል።

ቢቢሲ አነጋገርኳቸው ያላቸው የሆስፒታሉ የነርሲንግ አገልግሎት ኃላፊ ቴዎድሮስ ካህሳይ ከጦርነቱ በፊት ከትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ለሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ሆስፒታል አሁን ግን እጅግ መዳከሙን ገልጸዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው የሰሜኑ ጦርነት ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል እና ከዓለም ተቆራርጣ ባለችው ትግራይ ክልል በሕክምና ቁሳቁሶች፣ መድሃኒቶችን እና የሰብዓዊ እርዳታዎች እጥረት በርካቶች ለከፋ ችግር መዳረጋቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ የጤና ማዕከላት በአስፈላጊ መድኃኒት እጥረት ሳቢያ ሥራ ማቆማቸውን ያስታወቀ ሲሆን በትግራይ ክልል የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው ህፃናትን ጨምሮ ህሙማን በከፍተኛ መድኃኒት እጥረት ምክንያት እየሞቱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማድረስ ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታውቆ፤ የትግራይ ኃይሎች ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በኃይል ከያዟቸው የአጎራባች አፋር ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ ጠይቆ ነበር።

ይህን ተከትሎም የትግራይ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዳደረጉና ከአፋር ክልል ኤረብቲ መውጣታቸውን ገልጸዋል።

ነገር ግን በዚህ ሳምንት ሕወሓት ከአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ ለመውጣት ዘላቂ፣ ያልተገደበ፣ ወቅታዊ እና በቂ የሆነ እርዳታ ማቅረብን ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡን ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል የነርሲንግ አገልግሎት ኃላፊው ቴዎድሮስ ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ለሆስፒታሉ ሲሰጥ የነበረው ድጎማ እና የሕክምና ቁሳቁስ አነስተኛ እንደነበር አስታውሰው ላለፈው አንድ ዓመት ግን ሆስፒታሉ ካለምንም በጀት እየሠራ እንደሆነ ገልጧል፡፡

ኃላፊው እንደሚሉት ድጋፍ የተደረጉላቸው መድሃኒቶች በዓይነትም እጅግ አነስተኛ እንደነበር ጠቁመዋል።

አክለውም እንደ ካንሰር፣ ደም ግፊት ላሉ ስር የሰደዱ በሽታዎች ምንም ዓይነት መድሃኒት አለመግባቱን በመግለፅም ለሳንታት ታይቶ የነበረው የሆስፒታሉ አገልግሎት መሻሻል ተመልሶ መውረዱን አክለዋል።

ለላብራቶሪ የሚውሉ ግብዓቶች፣ መድሃኒቶች፣ ማሽኖችን ማንቀሳቀሻ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ተኝተው ለሚታከሙ የሚቀርብ ምግብ፣ ለሠራተኞች የሚከፈል በሌለበት መስራትም አስቸጋሪ አንደሆነ ቴዎድሮስ ገልጿል።

አስራ ስምንት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img