Friday, November 22, 2024
spot_img

የፓርላማ ተመራጩና የኦሮሚያ ብልጽግና አባሉ በከረዩ ለተፈጸመው የአባ ገዳዎች ግድያ የኦሮሚያ ክልል አመራሮችን ተጠያቂ አደረጉ

  • አቶ ታዬ ደንደአም የክልሉን አመራሮች በሙስና ወንጀል ከሰዋል

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 20 2014 በኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲን ወክለው ተወዳድረው የፓርላማ አባል የሆኑት አቶ ሀንጋሳ ኢብራሂም በቅርቡ በከረዩ ለተፈጸመው የአባ ገዳ ከድር ሀዋስ ቦሩ እና ሌሎች 13 የከረዩ ጉሳ አመራሮች ግድያ ተጠያቂው የክልሉ መንግስት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፓርላማ አባሉ ለግድያው በዋነኛነት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳን ተጠያቂ ናቸው ብለዋል፡፡ አቶ ሀንገሳ ኢብራሂም በግል የፌስቡክ ገጻቸው በቀጥታ ባሰራጩትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አመራሮችን በነቀፉበት ንግግራቸው «የከረዩ አባገዳዎችን አንበርክኮ ያስረሸነው መንግስት ነው፡፡ ትእዛዙን ያስተላለፈውም አራርሳ መርዳሳ የተባለ የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ሀንጋሳ ድርጊቱ እንዴት እንደተፈጸመ ሲያስረዱ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ «እናንተ መካከል ሁለት የሸኔ አባላት አሉ» በሚል የተሳሳተ መረጃ በእለቱ በማለዳ የከረዩ ማህረሰብ አባላቱን እንደከበበና በቦታውም አባገዳዎችን ጨምሮ 39 ሰዎችን ወስዶ በሰቃ የሚባል ጫካ ውስጥ 16ቱን አንበርክኮ ያለ ርህራሄ መግደሉን ገልጸዋል። በተጨማሪም «አስክሬናቸው ገምቶ እስኪሸት ድረስ ለአራት ቀናት እዚያው እንዲቆይም አድርገዋል» ብለዋል አቶ ሀንጋሳ በንግግራቸው።

«የከረዩ አባገዳዎችን አንበርክኮ ያስረሸነው መንግስት ነው፡፡ ትእዛዙን ያስተላለፈውም አራርሳ መርዳሳ የተባለ የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነው»

ከአቶ ሀንገሳ ቀደም ብሎም የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታና የቀድሞ የኦሮሚያ ብልጽግና ሕዝብ ግንኙነት የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ክስ በክልሉ መንግሥት አመራሮች ላይ ሰንዘረው ነበር። አቶ ታዬ ስም ባይጠቅሱም ድርጊቱ የተፈጸመው በክልሉ መንግሥት መሆኑን አልሸሸጉም።

የከረዩ አባ ገዳ ከድር ሃዋስ ቦሩን ጨምሮ በበርካታ ግለሰቦች ላይ ለተፈጸው ግድያ ኅዳር 24፣ 2014 በመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች መግለጫ ያወጣው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ‹‹አሰቃቂ›› ያለውን ግድያ የፈጸመው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ‹ሸኔ› ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡ ቢሮው በመግለጫው ቡድኑ በየቀኑ ንፁሃንን በአሰቃቂ ሁኔታ እየገደለ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያለውን ጭካኔ እያረጋገጠ ይገኛል ያለ ሲሆን፣ ጥቃቱን ካስተናገዱት መካከል ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ እና ሀደ ስንቄዎች እንደሚገኝበትም በመግለጫው አትቶ ነበር፡፡

ነገር ግን ለግድያው በክልሉ መንግስት ውንጀላ የቀረበበት ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚለውና በመንግስት «ሸኔ» በሚል ስም የሚጠራው ቡድን ቃል አቀባይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ኦዳ ተርቢ፣ ከክልሉ መንግስት መግለጫ አንድ ቀን ቀድሞ ኅዳር 23፣ 2014 በኦፌሴላዊ የትዊተር ገጹ ባሰራጨው ማስታወሻ፣ የክልሉ መንግስት በከረዩ የወታደር ምልመላ ለማድረግ ያደረገውን ሙከራ የአካባቢው ሽማግሌዎች ተቃውመውት ነበር ያለ ሲሆን፣ የክልሉ መንግስት ለዚሁ አጸፋ እርምጃውን ወስዷል ሲል መንግስትን ራሱን ወንጅሏል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የተናገሩት አቶ ሀንጋሳ ኢብራሂም፣ አባ ገዳ ከድር ሃዋስ ቦሩን ጨምሮ ሸኔ ናቸው በማለት የገደላቸው የክልሉ መንግስት መሆኑን ጠቅሰው፣ ጉዳዩን የያዘው የክልሉ የፖሊስ ኃላፊ «ሁሉንም ብትፈጇቸው ኖሮ መንግስት ነው የገደላቸው አንባልም ነበር» ማለቱን ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ መረጃ ይፋ ያደረጉትም ከግድያው የተረፉት ሁለት ሰዎች መሆናቸውን ነው አቶ ሀንጋሳ ጨምረው የገለጹት፡፡

የፓርላማ አባሉ አቶ ሀንገሳ በተጨማሪም በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ውስጥ በመዘፈቅ፣ በዘመድ አዝማድና በወንዜነት ጥቅማ ጥቅም፣ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈጸምና የገንዘብ ምዝበራ የክልሉን መንግሥት አመራሮች የወነጀሉ ሲሆን፣ አመራሮቹን ተጠያቂ ለማድረግ ይህ ብቻ በቂ ነው በማለት የፌዴራል መንግሥቱ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ መልኩ አቶ ታዬ ደንደአ የክልሉን አመራሮች ስም ሳይጠቅሱ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ተንሰራፍቷል ያሉትን ሙስና በፌስቡክ ገጻቸው በአሮሚኛ ቋንቋ ባሰራጩት ጽሑፍ ይፋ አድርገዋል። ችግሩ እስከሚስተካከልም እስከ መጨረሻ አመራሩን እንደሚታገሉ አሳስበዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ ብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች መካከል ከፍተኛ የፖለቲካ ልዩነቶች እያየሉ መምጣታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በተሰዘረባቸው ውንጀላ ላይ እስከአሁን የሰጡት ምላሽም ሆነ ማብራሪያ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img