Saturday, May 18, 2024
spot_img

ሕወሓት ተዋጊዎቹ በኮምቦልቻ የምግብ መጋዘን ዘርፈዋል መባሉን አስተባበለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 2፣ 2014 ― ከፌዴራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኘው ሕወሓት፣ ተዋጊዎቹ በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ዘርፈዋል መባሉን አስተባብሏል፡፡

ሕወሓት በውጭ ጉዳዮች ቢሮ በኩል ባሠራጨው መግለጫው፣ ኃይሎቹ ከሰሞኑ የኮምቦልቻ መጋዘን ዘርፈዋል በሚል በብዙኃን መገናኛዎች መረጃ ሲሠራጭ መመልከቱን በመጥቀስ፣ ኃይሎቼ እንኳን ሊዘርፉ ከተባለው ተቃራኒ ቤተሰቦቻቸው ጠኔ ውስጥ ወድቀው ጥበቃ ሲያደርጉ ነበር ብሏል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር የሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የአማራ ክልል ከተሞች በሆኑት ደሴና ኮምቦልቻ የነበሩት መጋዘኖቹ በሕወሓት ኃይሎች መዘረፋቸውን ተከትሎ በአካባቢዎቹ የምግብ እርዳታ አቋርጫለሁ ያለው ከሁለት ቀናት በፊት ነበር፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱያሪክ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ የሕወሓት ኃይሎች በዓለም ምግብ ፕሮግራም የነበሩ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ሕጻናት የሚቀርቡ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ አቅርቦት ክምችት ወስደዋል፡፡

የሕወሓት ታጣቂዎች የእርዳታ ምግብ ተከማችተውባቸው የነበሩት መጋዘኖቹን በዘረፉበት ወቅት በስፍራው በነበሩ ሠራተኞቹ መሳሪያ ተደግኖባቸው ስለነበር መከላከል ሳይችሉ መቅረታቸውንም የቢሮው እና የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ኃላፊ ዶ/ር ካትሪን ሶዚ በትላንትናው እለት በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ሆኖም ክሱ የቀረበበት ሕወሓት፣ ኃይሎቹ ጥበቃ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ለሚመለከተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል አሳውቄያለሁ ነው ያለው፡፡

በዝርፊያው ሰበብ እርዳታውን ማቋረጡን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ድጋፉን ለመቀጠል የሁኔታዎችን መሻሻል እንደሚጠብቅ በትላንትናው እለት ገልጧል፡፡

በመጋዘን የነበረ የእርዳታ እህል ተዘርፎባቸዋል የተባሉት የአማራ ክልል ከተሞች የሆኑት ደሴ እና ኮምቦልቻ ባለፈው ጊዜ በሕወሓት ቁጥጥር ስር ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ ሊጠናቀቅ ባለው ሳምንት መጀመሪያ ቀን በፌዴራል መንግስት የፀጥታ ቁጥጥር ስር ተመልሰዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img