Saturday, May 18, 2024
spot_img

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ – ‹ዘ ዊኬንድ›ን አምባሳደር አደረገ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 29፣ 2014 ― የዓለም ምግብ ፕሮግራም ታዋቂውን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ድምጻዊ አቤል ተስፋዬን (በሚታወቅበት የመድረክ ሥሙ ዘዊኬንድን) የበጎ አድራጎት አምባሳደሩ ማድረጉን በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሎስ አንጀለስ ባካሄደው ልዩ ሥነ ሥርዐት አቤል ተስፋዬ በመላው ዓለም ረሐብን ለማስወገድ ከሚታገሉ በጎ ፈቃደኛ የድርጅቱ አምባሳደሮች ጋር በጋራ እንደሚሠራ ነው የገለጸው፡፡

ከወራት በፊት በትግራይ ክልል በተነሳው ጦርነት ለተጎዱ ሰዎች የሚውል አንድ ሚሊዮን ዶላር ለዓለም ምግብ ፕሮግራም የለገሠው ዘ ዊኬንድ፣ በተያዘው ዓመት ብቻ የትግራዩን ጨምሮ ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ መስጠቱ ተነግሮለታል፡፡

ድምጻዊው በወቅቱ በይፋዊ የትዊተር ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ‹‹በኢትዮጵያ ከጨቅላ ሕጻናት እስከ አዛውንቶች በጭካኔ ሲገደሉ እና ከፍርሃት የተነሳ ቤታቸውን ጥለው ሲፈናቀሉ ስሰማ ልቤ ይሰበራል›› ብሎ ነበር፡፡

ከኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦች ካናዳ ውስጥ የተወለደው አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊኬንድ) በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሳው ጦርነት ተጽዕኖ አሳድሮበት ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የዓለም ምግብ ፕሮግራም በወቅቱ ከድምጻዊው ያገኘውን ስጦታ በትግራይ ክልል በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለው እርዳታ ለሚጠብቁ ዜጎች እንደሚያውለው ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ድጋፉ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 2 ሚሊዮን ዜጎች ለስድስት ወራት ምግብ ለማቅረብ እንደሚረዳውም አሳውቆ ነበር፡፡

በሙዚቃ ሥራዎቹ ከፍተኛ የሚባሉ የበርካታ ፕላቲኒየም እና ዳይመንድ ተሸላሚው ዘ ዊኬንድ በፖፕ ሙዚቃ ዝነኛ ከሆኑ ድምጻዊያን አንዱ ሲሆን፣ ስፖቲፋይ በተሰኘው የበይነ መረብ የሙዚቃ ማድመጫ መድረክ ላይ ከ86 ቢሊዮን ጊዜ በላይ በመደመጥ፤ ዘፈናቸው በርካታ ጊዜ ከተሰማላቸው ድምጻዊያን መካከል በዋናነት ይጠቀሳል።

አቤል ተስፋዬ ሁሉም ሙዚቀኞች አያገኙትም የሚባለውን አሜሪካውያን በከፍተኛ ትኩረት የሚከታተሉትን የስፖርት ውድድር ሱፐር ቦውልን ጨምሮ በታላላቅ መድረኮች ሥራውን ለማቅብ የበቃ የዘመኑ ኮከብ ነው።

አቤል አምባሳደር የሆነበት በተባበሩት መንግሥታት ስር የሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በየዓመቱ ከ80 በላይ በሆኑ አገራት ውስጥ የሚገኙ ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሕይወት አድን የምግብ ድጋፍ ያደርጋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በተለያዩ አገሮች ነፍስ አድን የምግብ እርዳታ የሚሰጥ ትልቁ ተቋም ነው። ፕሮግራሙ አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰብአዊ እርዳታ እያደረጉ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከልም ይጠቀሳል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img