አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 24፣ 2014 ― የሊቢያ ፍርድ ቤት የቀድሞ የአገሪቱ መሪ ሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ወደ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩነታቸው እንዲመለሱ ወስኗል፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የመጣው የሊቢያ ምርጫ ኮሚሽን ሳኢፍ አል ኢስላምን ጨምሮ ለምርጫው ሊወዳደሩ የነበሩ 25 ሰዎች ከምርጫው ውጭ እንዲሆኑ መወሰኑን ተከትሎ ይግባኝ በመጠየቁ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ሰይፍ አል ኢስላም በሀገሪቱ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይወዳደር የተላለፈውን መመርያ አንስቶ ለመወዳደር ፍቃድ እንደሰጠው ጠበቃው ኻሊድ አል-ዛይዲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
የሊቢያ ባለስልጣናት ሰይፍ አል ኢስላምን ከምርጫ ያስወጡት ከአስር ዓመት በፊት በአባቱ ላይ በተነሳው ሕዝባዊ አመጽ የጦር ወንጀል ፈጽሟል በሚል ነበር፡፡
ሰይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ በሊቢያ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከተመዘገቡ እጩዎች መካከል ለአሸናፊነት ከሚገመቱት መካከል እንደሚገኝ የተነገረለት ሲሆን፣ ከአባቱ ከስልጣን መነሳት በኃላ የሊቢያን አንድነት መመለስ እንደሚፈልግ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
በአገሪቱ ምርጫ ከወደ ምሥራቅ ሊቢያ የተገኙት ከሊፋ ሃፍታር፣ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሀሚድ ዲቤባህ እና የቀድሞ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፋቲ ባሻጋ እንደ ሰይፍ አል ኢስላም ሁሉ የሚጠበቁ እጩዎች ናቸው።