Sunday, May 5, 2024
spot_img

በነ ጃዋር መሐመድ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 24፣ 2014 ― የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት እነ ጃዋር መሐመድ በጠበቆቻቸው በኩል ያቀረቡት የመቃወሚያ አቤቱታ ላይ ዓቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥበት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ በፊት ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ነጻ የሚባሉ ግለሰቦች በአስፈጻሚ አካላት እየታሰሩ ነው የሚል ምክንያት በማቅረብ በፍቃዳችን ችሎት አንቀርብም ብለው ነበር፡፡

ጉዳያቸውን የሚከታተለው የስር ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ በሌሉበት ጉዳያቸው ይታይ ሲል ብይን የሰጠ ሲሆን፣ ይህንኑ ብይን አግባብ አይደለም ያሉት የተከሳሽ ጠበቆች አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ይግባኙን የሰማው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት በዛሬው ቀጠሮ አቤቱታቸውን መርምሮ መዝገቡ ያስቀርባል በማለቱ፣ በይግባኙ ላይ ዓቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥበት ለታኅሳስ 6፣ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ዓቃቤ ህግ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በመዝገቡ ተከሳሾች ላይ የሚሰሙ ምስክሮች ለደህንነታቸው ከምስክር ጥበቃ አዋጅ አንጻር 10 ምስክሮች በዝግ 136ቱ ምስክሮች ደግሞ ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙለት ያቀረበው አቤቱታ በስር ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉ ተከትሎ ምክንያቶቼ ሳይመዘን አቤቱታዬ ውድቅ መደረጉ አግባብነት የለውም ሲል በድጋሚ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ነበር።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቤቱታውን መርምሮ በምስክሮች ደህንነት ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋ በማሳያ አልቀረበም በማለት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንደማይነቀፍ በመግለጽ የዓቃቤ ህግ የይግባኝ አቤቱታውን አያስቀርብም ሲል ውድቅ አድርጎታል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img