Sunday, September 22, 2024
spot_img

በነ ዶ/ር ደብረጺዮን መዝገብ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 16፣ 2014 ― በነ ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል መዝገብ የተሰየመው ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው፣ ዶክተር ደብረጺዮንን ጨምሮ የ62 ተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ በላፕቶፕ የያዘው ጠበቃ ዘረሰናይ ወ/ሰንበት ከነላፕቶፑ በመታሰሩ ተቀብለን ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ሲሉ ጠበቆች መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።

በዛሬው ችሎት በመዝገቡ የተካተቱት ስብሐት ነጋ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፣ ዶ/ር አብርሐም ተከስተ፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱን ጨምሮ 21 ተከሳሾች አልተገኙም። ማረሚያ ቤቱ ታሳሪዎቹ ላለመቅረባቸው የሸዋ ሮቢት ታራሚዎች ወደ ዝዋይ በማዘዋወር ሂደት በመሆኑ ነው ሲል በጉዳይ አስፈጻሚው በኩል ገልጿል።

የተከሳሽ ጠበቆችም ማረሚያ ቤቱ ያቀረበው ምክንያት ተገቢ በመሆኑ እንደማይቃወሙ ገልፀዋል ነው የተባለው።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ቀጠሮ የተሰየመው የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ፣ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ትገኛለች የተባለችውን 20ኛ ተከሳሽ የቀድሞ የትግራይ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ሃላፊ አሰፉ ሊላይ ፌደራል ፖሊስ በችሎት እንዲያቀርባት የተሰጠውን ትዛዝ ለመጠባበቅ እንዲሁም ዓቃቤ ሕግ ዶ/ር ደብረጺዮን እና ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ያልተያዙ ተከሳሾችን የሀገር መከላከያ ሰራዊት በልዩ ትዛዝ ይዞ እንዲቀርባቸው ትዛዝ ይሰጥልኝ ሲል በጠየቀው ጥያቄ ላይ ትዛዝ ለመስጠት በተጨማሪም የ44ኛ ተከሳሽ በምርመራ ወቅት የተያዘብኝ ሰነዶች ይመለስልኝ አቤቱታ ላይ ትዛዝ ለመስጠት ነበር።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ባለመቅረባቸው ምክንያት በዓቃቤ ህግና በ44ኛ ተከሳሽ የቀረቡት አቤቱታዎች ላይ በቀጣይ ቀጠሮ ተከሳሾቹ ባሉበት ትዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል።

ትዕዛዝ ያልተሰጠባቸው አቤቱታዎች ላይ ትዕዛዝ ለመስጠትና የተከሳሾቹን የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅም ለታኅሣሥ 21፣ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img