አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 7፣ 2014 ― በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ ቦረና እና አቶ ደጀኔ ጣፋ በሌሉበት ምስክር እንዲሰማ ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን ጠበቆቻቸው ተቃውመውታል፡፡
የስር ፍርድ ቤት እነ ጃዋር መሐመድ በሌሉበት ምስክር እንዲሰማ ብይን የሰጠው ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት አንቀርብም ማለታቸውን ተከትሎ ነበር፡፡
ነገር ግን የታሳሪ ጠበቆች፣ እነ ጃዋር በሌሉበት ምስክር እንዲሰማ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ብይን በመቃወም 5 ነጥቦችን ጠቅሰው የይግባኝ አቤቱታ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አስገብተዋል።
የነ ጃዋር መሐመድ ጠበቆች ለፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ካሰፈሩት መካከል፣ ‹‹በፍርድ ቤት የሚፈቱ ግለሰቦች በአስፈጻሚ አካላት እየታሰሩ ስለሆነ›› ደንበኞቻው ፍርድ ቤት አንቀርብም ያሉበትን አቤቱታ የስር ፍርድ ቤቱ ሳይመረምር በሌሉበት ይሰማ ማለቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሾች አንቀርብም ቢሉም በሥነ ሥርአት ሕጉ መሰረት አስገድዶ ማቅረብ እየተቻለ በሌሉበት መባሉ አግባብ የለውም ያሉት ጠበቆች፣ በሌሉበት ቢባል እንኳ አስቀድሞ ለተከሳሾች ተነግሯቸው እንዲያውቁት ሊደረግ እንደሚገባ፣ ትእዛዙ ለየትኛው ክርክር እንደሆነ በግልጽ አለመቀመጡን እንዲሁም በማረሚያ ቤት እያሉ በሌሉበት መባሉ ስርአትን የተከተለ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አቤቱታው የቀረበበት ፍርድ ቤት፣ አቤቱታውን መርምሮ ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለውን ትዛዝ ለመስጠት ለኅዳር 24፣ 2014 ቀጥሮ ሰጥቷል።