Friday, November 22, 2024
spot_img

በመተከል እና ካማሺ ዞኖች ከባለፈው እሑድ ጀምሮ ውጊያ በመካሄድ ላይ መሆኑን ኢሰመኮ አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 21፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል እና ካማሺ ዞኖች ከእሑድ መስከረም 16 ጀምሮ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ኃይሎቹ መካከል “ውጊያ” በመካሄድ ላይ መሆኑን አሳውቋል፡፡

ይህንኑ ተከትሎም ከመስከረም 19 ጀምሮ ነዋሪዎችን ወደ ዳሊቲ ከተማ ለማሸሽ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመለከተው ኮሚሽኑ፣ ይሁንና የሴዳል ወረዳ አመራሮችም ሆነ ከወረዳው የሸሹ ነዋሪዎች በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል ብሏል፡፡

ኢሰመኮ የአካባቢዎቹ የፀጥታ ሁኔታና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ በፌዴራል መንግስቱና በአካባቢው ኮማንድ ፖስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በተሻለ ፍጥነት ሊተገበሩና ሊጠናከሩ እንደሚገባ ባሳሰበበት መግለጫው፣ ከመስከረም 14 ጀምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች “የጉሙዝ ታጣቂዎች” ብለው የሚጠሯቸው ኃይሎች በሴዳል ወረዳ የሚኖሩ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ወደ 145 የሚገመቱ የጉሙዝ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰዎችን ማገታቸውን አሳውቋል፡፡

ታጣቂዎቹ ሲቪል ሰዎችን ያገቱት “ዓላማችንን አልደገፋችሁም” በሚል ምክንያት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለምዶ “መርሻው” እና “ኤክፈት” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ እንዳገቷቸውም ተነግሯል፡፡  

ከታጋቾቹ መካከል “ቢያንስ ሁለት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውንና” ቀሪው “በአስከፊ ስቃይ ውስጥ የተያዙ” መሆናቸው ሲገለጽ፣ በመስከረም 14 ጀምሮ በደረሰው ጥቃት ምክንያት ወደ 5 ሺሕ የሚሆኑ ተጨማሪ የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለጊዜው በወረዳው መስተዳደር ግቢ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ መሆናቸውንም ኮሚሽኑ ገልጧል፡፡

ኢሰመኮ በመግለጫው ማሳረጊያ በክልሉ በካማሺ እና በመተከል ዞኖች በተደጋጋሚ የሲቪል ሰዎችን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት አደጋ ላይ የጣሉ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቢቆዩም፣ በፌዴራል እና ክልል መንግሥታት የተወሰዱት እርምጃዎች አደጋውን ለመቀልበስ እና የሲቪል ሰዎችን ሕይወት ከሞት ለመታደግ በቂ ባለመሆናቸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁለንተናዊ መፍትሔ የማፈላለጉ ሂደት አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥልእንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img