አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 14፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ባለፈው ሳምንት መስከረም 7 እና 8 በደረሱ ሦስት ተያያዥ ጥቃቶች 18 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን አሳውቋል፡፡ በተጨማሪም መስከረም 8 በውልማይ ቀበሌ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውንም ኮሚሽኑ ገልጧል፡፡
በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ የሚገኙ ሲቪል ዜጎች ለደህንነታቸው አስጊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ያለው ኮሚሽኑ፣ ከዚህ ውጭ ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ከተለያዩ የወረዳው አካባቢዎች ተፈናቅለው በኖሌ ቀበሌ፣ በሀሮ እና ኪራሙ ከተሞች ተጠልለው የሚገኙ ከ40 ሺሕ በላይ ዜጎች ለወራት አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እና ሌሎች ድጋፎች ባለማግኘታቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አሳውቋል፡፡
በዚሁ ሰበብ አሁኑ ወቅት ኪራሙ ወረዳን ከነቀምቴና ከቡሩ የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች ለተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ተዘግተው እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ኢሰመኮ የፌዴራሉ እና የክልሉ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች በኪራሙ ወረዳ ላለው የፀጥታ ስጋት ሰዘላቂ መፍትሄ በመስጠት በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱ ሃይሎችን ከሕግ ፊት በማቅረብ ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳስቧል፡፡