Monday, October 7, 2024
spot_img

ለ39 ዓመታት ራሱን ስቶ የቆየው የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አረፈ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጳጉሜን 2፣ 2013 ― ላለፉት 39 ዓመታት ኮማ ውስጥ የነበረው የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጫዋች ዣን ፒየር አዳምስ በ73 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

ዣን ፒየር አዳምስ ሆስፒታል የገባው እአአ ግንቦት 1982 ለጉልበት ቀዶ ሕክምና የነበረ ሲሆን፣ ማደንዘዣ ሲሰጠው በተፈጠረ ስህተት ምክንያት ራሱን ከሳተ በኋላ ለ39 ዓመታት ከኮማ አልነቃም።

ትውልዱ ሴኔጋል የሆነው የፊት አጥቂው ዣን ፒየር፤ በፈረንሳይ ለፓሪስ ሴንት ዠርሜን እና ኒይስ ቡድን ከ140 ጊዜ በላይ ተሰልፏል።

ዣን ፒየር ወደ ሆስፒታል የተወሰደው በልምምድ ላይ ሳለ ጉልበቱ ላይ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ነበር፡፡ በእለቱ በሆስፒታሉ የነበሩ አብዛኞቹ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ላይ ስለነበሩ፣
ማደንዘዣ የሚሰጡት ሐኪም ዣን ፒየርን ጨምሮ ለስምንት ህሙማን አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበረ ነው የተገለጸው፡፡

ማደንዘዣ የሚሰጡትን ሐኪም የሚረዳ ተለማማጅ ባለሙያም ሆስፒታሉ ውስጥ ቢኖርም፣ ተለማማጁ ባለሙያ ኋላ ላይ ለዣን ፒየር ሕክምና የመስጠት አቅም እንዳልነበረው ተናግሯል።
ኋላም ማደንዘዣ የሚሰጡት ሐኪም እና ተለማማጁ ባለሙያ በሠሩት ስህተት ምክንያት ዣን ፒየር የልብ እና የአዕምሮ ጉዳት ደርሶበታል።

ሁለቱ ባለሙያዎች እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ድረስ ለስህተታቸው ሳይቀጡ ቢቆዩም፤ ኋላ ላይ 750 ዩሮ ቅጣት እንዲከፍሉ እና ለአንድ ወር ከስራ እንዲታገዱ ተወስኗል።

ዣን ፒየር ከ15 ወራት በኋላ ከሆስፒታል ወጥቶ ባለቤቱ በርንዴት በቤታቸው ውስጥ ስትንከባከበው ቆይታለች።

ለአራት አስርት ዓመታት ራሱን ስቶ ቢቆይም፤ ባለቤቱ ግን እስትንፋስ የሚሰጠው መሣሪያ እንዲቋረጥ አልፈቀደችም።

በየቀኑ ልብሱን እየቀየረችለት፣ ምግብ እያዘጋጀችለት፣ ስጦታ እየሰጠችው እና እያዋራችው 39 ዓመታትን ያሳለፈች ቢሆንም፣ ዣን ፒየር ኮማ ውስጥ ስለነበረ ለባለቤቱ ምንም ምላሽ ሳይሰጣት ቆይቷል። የሕክምና እርዳታ ይሰጡ የነበሩ ነርሶች እንደሚሉት ከሆነ፤ በርንዴት ከአጠገቡ ስትለይ ራሱን ስቶ የቆየው ዣን ፒየር አንዳች የስሜት ለውጥ ይታይበት ነበር።

የሕክምና ስህተት የሠራው ሆስፒታል እስከ ዛሬ ድረስ ይቅርታ አለመጠየቁ የዣን ፒየርን ባለቤት ዘወትር ያበሳጫት እንደነበርም ይነገራል፡፡

ኅልፈቱን በተመለከተ የቀድሞ ክለቩ ፓሪስ ሴንት ዠርመን ባወጣው መግለጫ፤ “ግርማ ሞገስ ያለው፣ ልምድ ያካበተው እና የተከበረው” ሲል ተጫዋቹን ገልጾታል፡፡ ሌላኛው የፈረንሳይ ክለብ ኒይስ በበኩሉ ለተጨዋቹ መታሰቢያ መርሃ ግብር እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል መባሉን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img