Saturday, May 4, 2024
spot_img

መንግሥት የፕሬስን ነጻነት ያክብር!

በትናንትናው እለት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአዲስ ስታንዳርድ ሚዲያ ባለቤት የኾነው የጃኪን አሳታሚን ፈቃድ መንጠቁን አሳውቋል። ባለሥልጣኑ እግዱን ተከትሎ በትዊተር ገጹ እንዳሳወቀው፤ ሚዲያው «አንድን የሽብር ቡድን «የመከላከያ ኃይል» በሚል በመጥራቱ እግዱ ተላልፎበታል ብሏል።

ጃኪን አሳታሚ ከአስር ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየና ከዚህ ቀደም በነበረው የኢሕአዴግ መንግሥት የመጽሔት ኀትመት ሥራው በመንግሥት ተቋርጦበት እንደነበረም ይታወቃል።

ከአዲስ ስታንዳርድ እግድ ሳምንታት በፊት የአውሎ ሚዲያ ፈቃድ መሰረዙንና፣ የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞችን ጨምሮ 14 የሚዲያዎቹ ባልደረቦች መታሰራቸውን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ተቋም ሲፒጄ በመግለጫው ማሳወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ አምባ ዲጂታልም በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ዘገባ ሠርቷል።

በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች ከታሠሩ ሁለት ሳምንታት በላይ ቢቆጠሩም፣ እስከአሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ከመኾኑም በላይ፣ አዋሽ አርባ በተባለ ለእስር አስቸጋሪ በሆነ ቦታ መታሰራቸው አሳሳቢ ነው።

አምባ ዲጂታል ሚዲያ መንግሥት በጋዜጠኞችና በሚዲያዎች ላይ እየወሰዳቸው ያሉት ተከታታይ እርምጃዎች እንደሚያሳስቡት ለማሳወቅ ይወዳል።

የፕሬስ ነጻነት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 29 የተረጋገጠና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈረመቻቸው ቃል-ኪዳኖችም የተደነገገ ነው።

የፕሬስ ነጻነት ከመሠረታዊ የሲቪል መብቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚታይና፣ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ዴሞክራሲያዎች መብቶችን በሚደነግገው ክፍል ውስጥ በቀዳሚ አንቀጽነት የተጠቀሰ ነው። መንግሥት ይሄን የፕረስ ነጻነት ያለ ምንም ተጨማሪ ጫና እንዲያከብር አምባ ዲጂታል ይጠይቃል።

የግሉ ሚዲያ ሴክተር በቀዳሚው የኢሕአዴግ መንግሥት ተደጋጋሚ ጡጫ ሲደርስብት የቆየ መሆኑ ይታወቃል።

የግል ፕሬሱ በሀገራችን 30 ዓመታት የሚደርስ እድሜ ቢኖረውም የሞያ እና የአቅም ጉድለትን ጨምሮ በመንግሥት በተደጋጋሚ በሚዲያዎቹና በጋዜጠኞቹ ላይ ሲወስድ በቆየው እርምጃ በሚገባው መጠን ማደግ ሳይችል ቀርቷል። በኢትዮጵያ እጅግ እየተመናመነ የመጣውን የግሉን ሚዲያ ሴክተር መንግሥት ከማቀብ ይልቅ፣ መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባው አምባ ዲጂታል ያምናል።

በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 19 ንኡስ አንቀጽ 3 መሠረት በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው እንዲከበር ይጠይቃል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img