አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሐምሌ 12፣ 2013 ― በሕግ ጥላ ሥር ከዋሉ 20ኛ ቀናቸውን ያስቆጠሩት 14 የበይነ መረብ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሠራተኞች ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፍትሃ ብሔር ችሎት ባስገቡት ማመልከቻ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ መመስረታቸው ተሰምቷል።
አቤቱታውን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ ለፌደራል ፖሊስ መጥሪያ እንዲደርሰው ልኳል።
ቢቢሲ የተከሳሾች ጠበቃ ታደለ ገብረ መድህን ነግረውኛል እንዳለው የፌደራል ፖሊስ መጥሪያውን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሳያደርሱ ተመልሰዋል።
ጠበቃ ታደለ “የመዝገብ ቤት ሠራተኞች በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ እንድንወጣ ተነግሮናል” ብለዋል።
ስለጉዳዩ የተጠየቁት የፌደራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ የለኝም ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ለፍትሃ ብሔር ችሎት የቀረበው አቤቱታ ከያየሰው ሽመልስ ውጪ ያሉት 13 አመልካቾች ከሰኔ 23 እስከ ሰኔ 25፣ 2013 በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ማረፊያ ቤት ተይዘው መቆየታቸውን ያመለክታል። ያየሰው ሰኔ 25 በቁጥጥር ሥር ውለው በተመሳሳይ ማረፊያ ቤት መግባታቸውንም አቤቱታው ጠቅሷል። ከሰኔ 25 በኋላ ተከሳሾችን ለመጠየቅ የሄዱ ቤተሰቦች ‘ተለቀዋል’ የሚል መረጃ እንደተሰጣቸውና እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡም ማመልከቻው ያሳያል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያሉበትን ሁኔታ ለመጎብኘት ጥረት ቢያደርግም ፈቃድ አለማግኘቱን እና ቤተሰቦችም ያሉበትን እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል።
“በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸው የአካል ደህንነት እና ነፃነት መብትን የሚጋፋ ተግባር ነው” የሚለው አቤቱታው ሁለት ፍርዶችን ጠይቋል።
“አመልካቾች በተጠሪ አማካኝነት የት ተወስደው እንደታሰሩ ገለልተኛ በሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አማካኝነት ተጣርቶ እንዲቀርብ” የሚለው ቀዳሚ ጥያቄያቸው ነው።
ሌላኛው “ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ ከ 48 ሰዓታት በላይ ታስረው በመቆየታቸው የአካል ነፃነታቸው እንዲከበርላቸው ይታዘዝልን” የሚል ነው።
አካልን ነፃ የማውጣት ክስ አንድ ሰው በሕግ ጥላ ሥር ውሎ በተገቢው ሰዓት ለፍርድ ሳይቀርብ ሲቀር በግለሰቡ አቤቱታ፣ በጠበቃው ወይም በሕግ ተወካዮቹ አማካኝነት የአካል ደህንነቱ ተጠብቆ ነፃ እንዲወጣ ለፍርድ ቤት የሚያመለክትበት ሥርዓት ነው።
ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ዛሬ ከሰአት በኋላ ይመለከታዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮ-ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች አያያዝ በሕግ አግባብ ሊሆን እንደሚገባው ማስታወቁ ይታወሳል።