አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 19፣ 2013 ― ባለፈው ዓመት ግንቦት ሚኒሶታ ውስጥ አፍሪካ አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል ወንጀል የተከሰሰው አሜሪካዊው ነጭ የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ቻውቪን 22 ዓመት ከስድስት ወር እስር ተፈርዶበታል፡፡
የዴሪክ ቻውቪን ቅጣት ‹‹የተጣለበትን እምነት እና ኃላፊነት በማጉደል እንዲሁም በታየው ልዩ ጭካኔ›› ላይ የተመሠረተ መሆኑን ዳኛው ተናግረዋል።
የፍሎይድ ቤተሰቦች እና ደጋፊዎቻቸው ውሳኔውን በደስታ ተቀብለዋል። ጠበቃው ቤን ክሩም በትዊተር ገጻቸው ‹‹ይህ ታሪካዊ ቅጣት ተጠያቂነትን በማስፈን የፍሎይድ ቤተሰቦችን እና አገራችንን ወደ ፈውስ አንድ እርምጃ እንዲጠጉ ያደርጋቸዋል›› ብለዋል።
የፍሎይድ እህት ብሪጅት ፍሎይድ ውሳኔው ‹‹የፖሊስ ጭካኔዎች በመጨረሻም በደንብ እየታዩ መሆናቸውን ቢያሳይም ገና ብዙ የሚቀር መንገድ አለ›› ብለዋል።
ቅጣት የተበየነበት ቻውቪን በበኩሉ ለፍሎይድ ቤተሰቦች ሐዘኑን መግለጹን ለፍርድ ቤቱ አስታውቆ ‹‹ለወደፊቱ ሌላ መረጃ ይኖራል። ነገሮች ትንሽ የአእምሮ ሰላም ይሰጣቸዋል›› ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ መግለጹን የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል፡፡ ሆኖም ግን ለድርጊቱ ይቅርታ አልጠየቀም።
ፍርድ ቤት የተገኙት የቻውቪን እናት ካሮሊን ፓውለንቲ በበኩላቸው ‹‹ሁልጊዜም በንጹህነትህ አምናለሁ። ከዚህ ሃሳቤ ስንዝር ፈቀቅ አልልም›› ሲሉ ስለ ልጃቸው ተናግረዋል፡፡
የቻውቪን ቅጣት ‹‹የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ላይ እስካሁን ድረስ የተላለፈ በጣም ረዥሙ ቅጣት ነው›› ሲሉ የሚኒሶታ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኬት ኤሊሰን ገልጸዋል፡፡