አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሚያዝያ 20፣ 2013 ― በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ተኮላ አይፎክሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን እንዲመሩ መሾማቸው ተሰምቷል፡፡ አዲሱ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ተኮላ ከትላንት ሚያዚያ 19 ጀምሮ መሾማቸውን ቢቢሲ ከራሳቸው አረጋግጫለሁ ብሎ ዘግቧል፡፡
አዲሱ ኮሚሽነር አቶ ተኮላ ከሦስት ዓመት በፊት በፌደራል ፖሊስ ውስጥ በኃላፊነት ከመመደባቸው አስቀድሞ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ቦታዎች ማገልገላቸው ተነግሯል፡፡
ከዚያ በፊትም በደቡብ ወሎ ዞን የኮምቦልቻ ከተማ ፖሊስ አዛዥ፣ የአምባሰል ወረዳ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ሠርተዋል።
በተጨማሪም አቶ ተኮላ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ዋና ኮሚሽነር የነበሩ ሲሆን በሠላም ማስከበር ሥራ ላይም ተሰማርተው የበኩላቸውን ተወጥተዋል።
የፌደራል ፖሊስ መሥሪያ ቤትን ከተቀላቀሉ በኋላም በምርመራ ቢሮ፤ የፋይናንስ እና ሎጂስቲክስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ሆነው አገልግለዋል። አዲሱ የፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ተኮላ አይፎክሩ በሠላም እና ደኅንነት የማስተርስ ዲግሪ እንዳላቸውም ነው የተሰማው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ተኮላ አይፎክሩ የተኩት የክልሉን ፖሊስ በኮሚሽነርነት ከሁለት ዓመታት በላይ የመሩትን አበረ አዳሙን ነው፡፡
አዲሱ ኮሚሽነር በቅርቡ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና በተፈፀሙ ጥቃቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ ነው ወደ ኃላፊነት የመጡት።