Monday, October 7, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በደሴ ቅርንጫፉ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሞብኛል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 12 2014 ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በደሴ ከተማ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ እንደወደመበት አስታውቋል፡፡

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ የመድኃኒት አቅራቢው ኤጀንሲን መረጃ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በደሴ ከተማ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥበት በነበረው የኤጀንሲው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የነበሩ በርካታ መድኃኒቶችንና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ያወደመው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኛነት የተፈረጀው ሕወሓት ነው፡፡

ይህንኑ በደሴ ከተማ በሚገኘው የኤጀንሲው ቅርንጫፍ በርካታ ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች በሕወሓት ቡድን መውደማቸውንና መዘረፋቸውን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አወል ሐሰን እንደነገሩት ጋዜጣው አስነብቧል፡፡

በርካታ የኤጀንሲው ንብረቶችና መድኃኒቶች በታጣቂ ቡድኑ መዘረፋቸውን አረጋግጫለሁ ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የንብረቶቹ ዋጋ በብር ሲተመን 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚገመት መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

ታጣቂ ቡድኑ የደሴን ከተማ ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ የሕክምና መድኃኒቶችን፣ እንዲሁም ቁሳቁሶችን መዝረፉንና ማውደሙን የጠቆሙት አቶ አወል፣ ይህ ውድመት ቀላል የማይባል የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚያስከትል ነው ያመላከቱት።

አያይዘውም፣ የመድኃኒቶቹን ቁጥር በውል ማወቅ ባይቻልም በዋናነት የጤና ፕሮግራም መድኃኒቶችና የመደበኛ መድኃኒቶች ወድመዋል ያሉ ሲሆን፣ የጤና ፕሮግራም መድኃኒቶች የሚባሉት ለኤች አይ ቪ ኤድስ በሽተኞች፣ ለእናቶችና ለተመሳሳይ በሽታዎች የሚሰጡ መድኃኒቶችን የሚያካትት መሆኑን አብራርተዋል።

የሕወሓት ታጣቂ ቡድን መውሰድ የሚችለውን ዘርፏል፣ ሌሎቹን ንብረቶች ደግሞ አውድሟል የሚሉት አቶ አወል፣ የእናቶችና የሕፃናት የክትባት መድኃኒት ማቀዝቀዣ መጋዘን፣ እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶች ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ነው ያሉት። ከዚህም በተጨማሪ፣ በቅርንጫፉ የነበሩ ኮምፒውተሮች በሙሉ ተዘርፈዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ከመድኃኒት አቅራቢ ቅርንጫፉ ውድመት በተጨማሪ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ከኹለት ሺሕ 700 በላይ የጤና ተቋማት ወድመዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img